ሐሙስ ጥቅምት 1 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ መካከል የሚደረገው ሦስተኛው ዙር የሦስትዮሽ ድርድር፤ በሚቀጥለው ሳምንት በካይሮ እንደሚካሄድ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታውቋል፡፡
ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን በግድቡ ዙሪያ አለመግባባታቸውን ለመፍታት ካሳለፍነው ነሃሴ ወር ጀምሮ ውይይት በማድረግ ላይ መሆናቸው ይታወቃል።
ከዚህ ቀደም በነሃሴ ወር ላይ የግድቡ ተደራዳሪ የቴክኒክ ባለሙያዎች በግብጽ ካይሮ ተገናኝተው የተወያዩ ሲሆን፤ ኹለተኛው ዙር የቴክኒክ ባለሙያዎች ውይይት ደግሞ ከኹለት ሳምንታት በፊት በአዲስ አበባ መካሄዱ ይታወሳል፡፡
በዚህም መሰረት በኹለተኛው ዙር ውይይት ላይ ሦስተኛው የአገራቱ ድርድር ጥቅምት ወር ላይ በግብጽ ካይሮ እንዲካሄድ ስምምነት ላይ መደረሱን ተከትሎ፤ ድርድሩ የፊታችን ጥቅምት 11 እና 12/2016 በግብጽ መዲና ካይሮ እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡



