ሐሙስ ጥቅምት 1 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በሥራ ፈጠራ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ላይ ትኩረቱን ያደረገውና “እንቆጳ” የተሰኘው ጉባዔ በዛሬው ዕለት በሚሊኒየም አዳራሽ ተከፍቷል።
ለተከታታይ ኹለት ቀናት የሚቆየው ይህ የኢንዱስትሪ እና የአመራር ተኮር ጉባዔ፤ ወሳኝ በሆኑ የሥራ ፈጠራ እና የኢኖቬሽን መሪ ሃሳቦች ላይ የሚያጠነጥን ሲሆን፤ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ላይ የራሱን አሻራ እንደሚያኖር ታምኖበታል።
በጉባዔው ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የዘርፉ ምሁራን፣ ከ150 በላይ ዓለም አቀፍ እና የአገር ውስጥ ተናጋሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች፣ የዓለም አቀፍ ኮርፖሬሽኖች እንዲሁም ኢንቨስተሮች ተሳትፈውበታል፡፡
“እንቆጳ ሰሚት” የአገር ውስጥ እና የክልል ውሳኔ ሰጪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ባለሙያዎች፣ የፈጠራ ባለሙያዎች፣ አካዳሚዎች፣ ባለሀብቶች እና የድርጅት መሪዎችን በማሰባሰብ፤ ዓላማ ላይ ያተኮሩ ውይይቶችን ለማመቻቸት ያለመ መሆኑም ተነግሯል፡፡
በዚህም ጉባዔው ትስስሮችን እና በጋራ መስራትን በማበረታታት ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን መላውን የአፍሪካ አህጉር የሚቀርጹ ሥራዎችን መፍጠር እና ማፋጠን ላይ ትኩረቱን እንደሚያደርግ ተገልጿል።
ይህን ጉባኤ ሎውሬንዶ እና አሶስዬትስ ከፍሎውለስ ኤቨንትስ ጋር በመተባባር እንዲሁም፤ በኢፌዲሪ ሥራ እና ክህሎት ሚንስቴር ድጋፍ ሰጪነት አዘጋጅተውታል፡፡



