ሐሙስ ጥቅምት 1 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አዲስ የሚያስገነባውን የዋና መስሪያ ቤት ባለ 62 ወለል ሕንጻ ዲዛይን፤ የአረንጓዴ ሕንጻ የወርቅ ደረጃ ሰርትፊኬት እንዲያገኝ በሚያስችል መልኩ እየተሥራ መሆኑን ፕሮጀክት ጽ/ቤቱ አስታወቀ፡፡
የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ በኃይሉ ታደለ እንደገለጹት፤ የተቋሙ ሕንጻ ዲዛይን በአሜሪካ የአረንጓዴ ሕንጻዎች ካውንስል በሚመራው የኢነርጂና የአካባቢ ዲዛይን (LEED) ሥርዓት መሰረት የወርቅ ደረጃ መስፈርቶችን የሚያሟላ ነው፡፡
የሕንጻው ዲዛይን ሃይል ቆጣቢ፣ በሰውና በአካባቢ ላይ ምንም አይነት ተፅዕኖ የማያሳድር እንዲሁም ለሥነ-ምህዳር ተስማሚ የሆኑ የአረንጓዴ ሥፍራዎች የተካተቱበት በመሆኑ የሚሰጥ የዕውቅና ሰርትፊኬት ነው ብለዋል።
ሜክሲኮ በሚገኘው በተቋሙ ቅጥር ግቢ የሚገነባው ባለ 62 ወለል ሰማይ ጠቀስ ሕንጻ ተቋሙን የሚገልፁ፤ ከፀሐይ እና ከንፋስ ኃይል በማመንጨት ለሕንጻው ፍጆታ ኃይል ማቅረብ የሚያስችሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች እንደሚኖሩት ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የአፈር ምርምር ሥራ ለማከናወን ከተመረጡት 28 ጉድጓዶች ውስጥ የ25ቱ ጉድጓዶች የቁፋሮ ሥራ መጠናቀቁን የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፤ የቀሪ 3 ጉድጓዶችን ቁፋሮ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡
አማካሪ ድርጅቱ የህንፃውን ዲዛይን ሙሉ በሙሉ አጠናቆ ለማስረከብ የስድስት ወር ጊዜ የተሰጠው ሲሆን፤ ሥራውም በተያዘለት ዕቅድ በጥራት እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የሕንጻውን ዝርዝር የዲዛይን ሥራ በታህሳስ ወር መጨረሻ ላይ በማጠናቀቅ ዋናውን ግንባታ የሚያከናውነውን ሥራ ተቋራጭ የመለየት ሥራ እንደሚሰራም መናገራቸውን ከተቋሙ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በ20 ሺሕ 792 ካሬ ሜትር ላይ የሚያርፈው እና የወለል ስፋት መጠኑ 197 ሺሕ 800 ካሬ ሜትር የሚሆነው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የዋና መስሪያ ቤት ሕንጻ ግንባታው ሲጠናቀቅ፤ 327 ነጥብ 5 ሜትር ርዝመት ይኖረዋል፡፡
ግንባታው 445 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚፈጅ ሲሆን፤ በ4 ዓመት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።



