መንግሥት የቆዳውን ዘርፍ ሙሉ ለሙሉ ረስቶታል ሲሉ የቆዳ ፋብሪካዎች ገለጹ

ሐሙስ ጥቅምት 1 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) መንግሥት የቆዳውን ዘርፍ ሙሉ ለሙሉ እንደረሳውና ትኩረት እየሰጠው እንዳልሆነ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የቆዳ ፉብሪካዎች ገልጸዋል፡፡

በሞጆ የሚገኘው የኮልባ የቆዳ ፉብሪካ የምርት ሥራ አስኪያጅ ሀብታሙ ሽፈራው፤ “መንግሥት የቆዳ ዘርፉ ላይ ትኩረት ባለመስጠቱ፤ ቀድሞ ከቆዳ ይገኝ የነበረው ገቢ እንዲታጣና ዘርፉም እንዲዳከም አድርጎታል፡፡” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡

መንግሥት በቆዳ ዘርፉ ዙሪያ ያወጣው አዋጅ ያለቀለት የቆዳ ምርት ብቻ ለውጪ ገበያ መቅረብ አለበት የሚል መሆኑ፤ የቆዳ ዘርፉን አደጋ ላይ ጥሎታል ያሉም ሲሆን፤ የመንግስት ውሳኔ አግባብ አይደለም ሲሉም ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የቆዳ ዘርፉን ወደ ምርት ለመቀየር የሚጠቀሙበት ኬሚካሎች በከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ የሚገቡ በመሆናቸው ትልቅ ተጽዕኖ መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም አገር ውስጥ የሚመረተው ኬሚካል ከሚፈለገው የኬሚካል ፍላጎት አንጻር አምስት በመቶ እንኳን የማይሸፍን መሆኑን አስረድተዋል።

“ለዚህም በአገራችን በተለያየ ጊዜ ኪሚካሎችን ለማምረት ሂደቶች ተጀምረው የነበረ ቢሆንም ሃላፊነት ወስዶ የሚሰራ ባለመኖሩ ተስተጓጉሎ ቀርቷል፡፡” ብለዋል፡፡

በዘርፉ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተሳትፎ ቢያደርጉ፤ 30 በመቶ እና ከዚያ በላይ ማምረት የሚያስችል አቅም ይኖር እንደነበርም ተመላክቷል፡፡

ለቆዳ ፋብሪካዎች መዳከም የጥራት ጉዳይ ሌላው ተግዳሮት መሆኑን ያነሱት ሥራ አስኪያጁ፤ “በአለም ዓቀፍ ደረጃ ከአንድ እስከ አራት ያሉ የቆዳ ደረጃዎች የሚፈለጉ ሲሆን፤ የእኛ ሀገር የቆዳ ምርቶች ጥራታቸው አራትና ከዚያ በታች ነው፡፡” ሲሉ ተናግረዋል።

እንዲሁም “መንግሥት የአገር በቀል የቆዳ ፉብሪካዎች እና የግል ባለሀብቶችን ከማበረታታት ይልቅ ለውጭ ኢንቨስተሮች የበለጠ ከለላና ድጋፍ እየሰጠ ነው፡፡” ሲሉ ገልጸዋል።

ይህም በድሬዳዋ፣ አዲስ አበባ እና ደብረብርሃን የሚገኙ አገር በቀል የቆዳ ፋብሪካዎችን ከገበያው ተገፍተው እንዲወጡ መደረጋቸውን ጠቁመዋል።

ለአብነትም ለ12 ዓመታት ሲሰራ የቆየው የደብረብርሃን የቆዳ ፋብሪካ በተዘጋበት ወቅት ሕጋዊ ያልሆኑ አካላት፤ የፋብሪካው ሰራተኞች ወደ ፋብሪካው እንዳይገቡ በማስፈራራት እንደመለሷቸውና ያለምንም ሕጋዊ መሰረት መዘጋቱን አመላክተዋል።

በሌላ በኩል የሆራ ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አሕመድ ኢብራሂም በበኩላቸው፤ ዘርፋ አደጋ ላይ መሆኑን ገልጸው፤ “ከመንግሥት በኩል ምንም አይነት ድጋፍ እያገኘን ካለመሆኑ ባሻገር ከመንግሥት ተቋማት የሚደርስብን ጫና ሌላው ተግዳሮት ነው፡፡” ብለዋል፡፡

ያለቀለት የቆዳ ምርት አምራቾችም ለሚያመርቱት ምርት በቂ የሆነ የቆዳ አቅርቦት አለመኖሩን በተደጋጋሚ ሲያነሱ የሚሰሙ እንዳሉ ተናግረዋል፡፡

ሆኖም ግን ጥሬ ቆዳን ሰብስበው የሚሸጡ ነጋዴዎች በበኩላቸው የሚቀበላቸው በማጣታቸው የሰበሰቡትን ቆዳ እየጣሉ መሆኑን በመግለጽ፤ በዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራበት ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here