አርብ ጥቅምት 2 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በሱዳኑ ጦርነት የተፈጸሙ ጥሰቶችን የሚያጣራ አለም ዓቀፍ አጣሪ ቡድን በድምጽ ብልጫ አቋቁሟል፡፡
የምክር ቤቱ ዉሳኔ የአፍሪካ የምክር ቤት አባላት ዘንድ ተቀባይነት ባይኖረውም፤ በተወሰነ የድምጽ ብልጫ ዉሳኔውን ማሳለፉም ተመላክቷል።
አጣሪ ቡድኑ የተቋቋመው፣ በ19 ድጋፍ፣ በ16 ተቃውሞና በ12 ድምጸ ተዓቅቦ ሲሆን፤ አጣሪ ቡድኑን የማቋቋሙ የውሳኔ ሃሳብ በድምጽ ያሳለፈው፣ ሱማሊያና ቻይና ሃሳቡን በመቃወማቸው መሆኑን ተገልጿል።
እንዲሁም አጣሪ ቡድኑ እንዲቋቋም የውሳኔ ሃሳብ ያቀረቡት፣ አሜሪካ፣ ብሪታንያና ኖርዌይ ሲሆኑ፤ የሱዳን መንግሥት ዓለም ዓቀፍ የጥሰት አጣሪ ቡድን የማቋቋሙን ሃሳብን እንደማይቀበል ባለፈው ሳምንት ማስታወቁ ተጠቁሟል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብት እና ሌሎች በርካታ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች፤ በሱዳን ግጭት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑት ኹለቱም ወገኖች አስገድዶ መድፈር፣ ማፈናቀል፣ ጅምላ ግድያ እና የመሳሰሉ ወንጀሎች ፈጽመዋል ማለታቸው ተመላክቷል።
ሱዳን የአጣሪ ቡድኑን መቋቋም ዉድቅ ያደረገች ሲሆን፤ የሱዳን የመከላከያ ሰራዊት በራሱ ወንጀለኞችን መቅጣት የሚችል ተቋም ነው ማለቷን ዘ ኢስት አፍሪካን ዘግቧል።
የዓለም አቀፍ ስደተኞች ድርጅት በሱዳን ጦርነት እስከ አሁን 5 ነጥብ 8 ሚልየን ያህል ሰዎች መፈናቀላቸውን የገለጸ ሲሆን፤ 1 ሚሊየን 237 ሺሕ 103 ያህሉ ወደ ኢትዮጵያ፣ ግብጽ፣ ሊቢያና ወደ ሌሎች ጎረቤት አገራት መሰደዳቸውም አስታውቋል።


