በቀጣይ ጊዜያት ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እንደሚኖር ተገለጸ

0
156

አርብ ጥቅምት 2 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በቀጣይ ጊዜያት ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እንደሚኖር ትንበያዎች ማመልከታቸውን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጅ ኢንስቲትዩት ገልጿል።

ኢንስቲትዩቱ በሚቀጥሉት አሥር ቀናት ዝናብ ሰጭ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች በአብዛኛው በደቡብና በደቡብ ምዕራብ የአገሪቱ ክፍሎች ላይ የተሻለ ገጽታ እንደሚኖራቸው የትንበያ መረጃዎች እንደሚያሳዩ አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም በጸሀይ ኃይል ታግዘው ከሚጠናከሩት የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ላይ በመነሳት፤ በተለይም በምዕራብና በጋ ኹለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የደቡብ አጋማሽ የአገሪቱ ክፍሎች ላይ የተስፋፋና ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ይኖራቸዋል ተብሏል።

በሌላ በኩል በመካከለኛዉ፣ በምስራቅ እና በሰሜን ምስራቅ የአገሪቱ ክፍሎች ላይ ከሚጠናከሩት የአየር ኹኔታ ክስተቶች ላይ በመነሳት፤ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እንደሚኖር አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች እንደሚያመላክቱ ገልጿል፡፡

በአጠቃላይ በሚቀጥሉት አሥር ቀናት ከኦሮሚያ ክልል ኹሉም የወለጋ ዞኖች፣ ጅማ፣ ኢሉባቦር፣ ቡኖ በደሌ፣ ኹሉም የአርሲ፣ የባሌና የጉጂ ዞኖች፣ ምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ፣ የቦረና ዞን፤ ከአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም፣ መካከለኛዉ፣ የሰሜንና የምዕራብ ጎንደር እንዲሁም የባህር ዳር ዙሪያ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖራቸው ተነግሯልል፡፡

በተጨማሪም በአዊ ዞን፣ የቤንሻንጉል ክልል ዞኖች፣ የሲዳማ ክልል ዞኖች፣ የመካከለኛዉ ኢትዮጵያ ክልል፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፣ ኹሉም የሱማሌ ክልል ዞኖች በተመሳሳይ መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ይኖራቸዋል ተብሏል፡፡

እንዲሁም የጋምቤላ ክልል ዞኖች፣ የደቡብ ጎንደር፣ የሰሜን ወሎ እና ምሥራቅ ጎጃም፣ የደቡብ ትግራይ ዞኖች፤ ሐረሪ እና ድሬደዋ በአንዳንድ ሥፍራዎቻቸው ላይ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በአብዛኛው ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ይጠበቃል።

በቀጣይ አስር ቀናት የሚኖረው እርጥበት በተለያየ ምክንያት ዘግይተው ለተዘሩና የእድገት ጊዜያቸውን ላልጨረሱ የመኸር ሰብሎች የውሃ ፍላጎት መሟላት ምቹ ኹኔታን ይፈጥራል የተባለ ሲሆን፤ እንዲሁም ኹለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት ጥምር ግብርና ለሚያካሂዱ ለደቡባዊው የአገሪቱ ክፍሎች ቀደም ብሎ የማሳ ዝግጅት ለማድረግና ዘር ለመዝራት ምቹ ኹኔታን እንደሚፈጥር ይጠበቃል፡፡

በሌላ በኩል ውሃ አጠር የሆኑ አካባቢዎች የሚገኘውን የዝናብ ውሃ ለመሰብሰብና ለማከማቸት መልካም አጋጣሚ ስለሚያገኙ ይህንኑ ለማከናወን የሚያስችል ዝግጅት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል፡፡

እንዲሁም በአንዳንድ የአገሪቱ አከባቢዎች የሚኖረው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ፤ በደረሱ ሰብሎች ስብሰባ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳያሳድር ከወዲሁ በየጣልቃው የሚኖረውን ደረቅ ቀናቶች በመጠቀም የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ በማንሳት አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጅ ኢንስቲትዩት አሳስቧል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here