“የሰማእታት የሃዘንና የክብር ቀን” ሥነ-ስርዓት በትግራይ ክልል እየተከናወነ ነው

0
186

ቅዳሜ ጥቅምት 3 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በፌደራል መንግስሥቱ እና በትግራይ ሀይሎች መካከል በተካሄደው ደም አፍሳሽ ጦርነት ወቅት ሕይወታቸው ያለፉ ተዋጊዎችን ለመዘከር፤ “የሰማእታት የሃዘንና የክብር ቀን” ሥነ-ስርዓት በትግራይ ክልል እየተከናወነ ይገኛል።

“የሰማእታት የሃዘንና የክብር ቀን” ሥነ-ስርዓቱ በመቀለ ከተማ በሰማዕታት መታሰቢያ ሐውልት እየተከናወነ ሲሆን፤ በሥነ-ስርዓቱ ላይ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ፣ የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገ/ማርያም (ዶ/ር)፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች፣ የሰማእታት ቤተሰቦች እንዲሁም በጦርነቱ ወቅት ጉዳት የደረሰባቸው ታጋዮች ተገኝተዋል።

በመታሰቢያ ሃውልቱ ላይም የክልሉ አመራሮች፣ የትግራይ ተወላጆች፣ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች እንዲሁም የተለያዩ አካላት የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል።

በተመሳሳይ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በጦርነቱ ወቅት መስዋዕትነት የከፈሉ የትግራይ ሰማዕታትን ለማሰብ ሻማ የማብራት እና ሌሎች ሥነ ስርዓቶች እየተካሄዱ ይገኛል።

በትግራይ ደረጃ የሚከናወነው “የሰማእታት የሃዘንና የክብር ቀን” ሥነ-ስርዓት ከትናንት ጥቅምት 2 ጀምሮ እስከ ጥቅምት 5/2016 ባሉት ሦስት ቀናት በተመሳሳይ ሰዓት በጊዜያዊ አስተዳደሩ ቁጥጥር ሥር ባሉ ኹሉም የክልሉ አካባቢዎች ይከናወናል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here