አርብ ጥቅምት 2 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይ.ኤም.ኤፍ የኢትዮጵያ መንግሥት የጠየቀውን የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት መውሰድ ባለበት ማሻሻያዎች ዙሪያ ከስምምነት ላይ ለመድረስ፤ በቀጣይ ሳምንታት ውይይት እንደሚያደርግ ትናንት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ድርጅቱ ትናንት ምሽት ባወጣው መግለጫ፤ የተቋሙ ልዑካን ቡድን ከመስከረም 14 እስከ 22/2016 ድረስ በአዲስ አበባ የአንድ ሳምንት ቆይታ አድርጎ በመስከረም ወር መጨረሻ ላይ መመለሱን ጠቅሷል።
ድርጅቱ የአገሪቱን የኢኮኖሚ መርሃ ግብር ማገዝ በሚችልበት ኹኔታ ዙሪያ ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር አወንታዊ እድገት የታየበት ውይይት ማድረጉንም አመላክቷል።
እንዲሁም መንግሥት የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠርና ጥብቅ የበጀትና የገንዘብ ፖሊሲ መከተሉን እንደ አዎንታዊ ርምጃዎች እንደሚወስደውም ገልጿል።
መንግሥት ለተያያዘው የኢኮኖሚ ፕሮግራም የሚያስፈልጉ ማሻሻያዎች ዙሪያ የሚካሄደው ውይይት በቀጣይ ሳምንታትም እንደሚቀጥል እና ከስምምነት ላይ ይደረሳል የሚል እምነት እንዳለውም ድርጅቱ በመግለጫው ጠቁሟል።
በፋይናንስ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ እና በብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ፤ በሞሮኮ እየተካሄደ ባለው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) እና የዓለም ባንክ የጋራ ዓመታዊ ጉባኤ ላይ መሳተፉ የሚታወስ ነው።
ልዑኩ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃግብር እንዴት ሊያግዝ ይችላል በሚለው ላይ ከተቋሙ ኃላፊ ጋር ውይይት ማድረጉም ተገልጿል።
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ኃላፊ ክርስታሊና ጆርጂቫ በኤክስ ገፃቸው (በቀድሞው ቲውተር) ከኢትዮጵያ ልዑክ ጋር ጥሩ ውይይት ማካሄዳቸውን ጠቅሰው፤ “ተቋማቱ በጦርነት፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በኢፍትሃዊነትና በሌሎች ምክንያቶች የተጎዳውን የዓለም ኢኮኖሚ ለማቃናትና ለማረጋጋት በሚያደርጉት ጥረት ለአፍሪካ ትኩረት እንሰጣለን። ” ሲሉ ከቀናት በፊት ገልጸዋል።
ኹለቱ ተቋማት በሞሮኮ ያደረጉት ዓመታዊ ጉባኤ ከ50 ዓመታት በኋላ በአፍሪካ የተደረገ የመጀመሪያ ስብሰባ ነው።



