እሁድ ጥቅምት 4 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) አባይና ቀይ ባህር የኢትዮጵያን ልማትና ጥፋት የሚወስኑ የኢትዮጵያ የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ናቸው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር በጣም እየጨመረ መሆኑን በማንሳት፤ አሁን ላይ አገሪቱ የግድ የባህር በር እንደሚያስፈልጋት ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አርብ ጥቅምት 2/2016 ምሽት፤ በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በተላለፈውና ‹‹ከጠብታ ውኃ እስከ ባሕር ውኃ›› የሚል ርዕስ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት ባደረጉት ገለጻ፤ ኢትዮጵያ የባህር በር የግድ እንደሚያስፈልጋት አበክረው ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በገለጻቸው፤ “የቀይ ባህርን ጉዳይ እኛ እንዴት ነው የምንመለከተው? ምንድን ነው እሳቤያችን? ይሄ እሳቤያችን ትክክል ነው ትክክል አይደለም? ያዋጣል አያዋጣም? መሆን አለበት መሆን የለበትም? በሚለው ጉዳይ ላይ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ከስሜት ነጻ በሆነ መንገድ አስልቶ፤ ለልጆቹ መልካም ነገር መተው አለበት” ያሉ ሲሆን፤ “በሕዳሴ ጉዳይ በተከዜ ጉዳይ እየተወያየን በቀይ ባህር ጉዳይ አንነጋገርም ካላችሁ አይሆንም” ሲሉም ለምክር ቤቱ አባላት ገልጸዋል፡፡
አክለውም፤ “በጉዳዩ ላይ ከአሁኑ መክረን አስበንበት አማራጭ ነገር የማናይ፤ የማይነሳ ጉዳይ ከሆነ አደገኛ ነው፡፡ ቢያንስ ድርጊቱ ቀርቶ እንወያይበት፡፡ አለበለዚያ የኢትዮጵያን ሕልውና አደጋ ውስጥ ያስገባል፡፡” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
“በአለም ላይ 120 ሚሊዮን ሕዝብ ኖሮት የባህር በር የሌላት አገር ኢትዮጵያ ብቻ ናት” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የኢትዮጵያ የሕዝብ ቁጥር እየበዛ ነው፡፡ አሁን ባለው አሰራር በተሸከምነው ልክ መሸከም አንችልም እየቆየ ሲሄድ ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ጉዳይ ይመጣል፡፡” ሲሉም አሳስበዋል፡፡
“ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ የባህር በር እንደነበራት ታሪክ ይናገራል። ስለዚህ እነዚህን የባህር በሮች በንግግር እና ውይይት ኢትዮጵያ ተጠቃሚ እንድትሆን ማድረግ አለብን፡፡” ያሉም ሲሆን፤ “እኛ ስጡን ብቻ አላልንም ከእኛም ውሰዱ ግን የባህር በር ያስፈልገናል ነው ያልነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ የወደብና የባህር በር አማራጮችን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ዘይላ፣ የጀቡቲ ወደብ፣ አዶሊስ፣ ምፅዋና አሰብን እንደ አማራጭ ማየት እንደሚቻል ገልጸው፤ “እኛ የግድ የአሰብ ካልሆነ ወይንም የግድ የምጽዋ ካልሆነ የሚል አቋም የለንም፡፡ እኛ የምንፈልገው መተንፈሻ በር ብቻ ነው” ብለዋል፡፡
አክለውም፤ “መተንፈሻ በር በየትኛውም ከመጣ በግዢም ይሁን፣ በሊዝም ይሁን በሆነ መንገድ በስምምነት ከመጣ የምንፈልገው እሱን ነው።” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
“ዋናው ችግር የሚመጣው እንዴት ነው የምንቀርበው የሚለው ጉዳይ ነው፡፡” ያሉም ሲሆን፤ “120 ሚሊየን ስለሆንኩ፣ ጉልበት ስላለኝ፣ መከላከያ ስላለኝ፣ አየር ስላለኝ፣ ሰው ደብድቤ፣ ገድዬ ነው የምቀርበው ያላችሁ እንደሆነ፤ እንደዛ ማድረግ የለብንም፤ በፍጹም በጉልበትና በጦርነት የባህር በር ይኑረን ብለን ጦር አንመዝም፡፡” ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
ለዚህም ከሕዳሴ ግድብ፣ ከአየር መንገድ፣ ከኢትዮ ቴሌኮም ድርሻ በመስጠት የባህር በር ድርሻ መውሰድን የመሳሰሉ አማራጮችን መጠቀም እንደሚቻል ለምክር ቤቱ አባላት አስረድተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ቀይ ባህርን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያም፤ “በታሪክ፣ በጂኦግራፊ፣ በዘር (በብሄር) እና በኦኮኖሚ ምክንያቶች የቀይ ባህር ጉዳይ ይመለከተናል።” ያሉ ሲሆን፤ “ቀይ ባህር ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ እንጂ ቅብጠት አይደለም። አባይና ቀይ ባህር የኢትዮጵያን ልማትና ጥፋት የሚወስኑ የኢትዮጵያ የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ናቸው።” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አክለውም፤ ከኢትዮጵያ ወደ ጎረቤት አገር የሚሄዱ የውሃ ሀብቶችን በማንሳት፤ “ማነው ከኢትዮጵያ ውሃ የማይወስደው ኹሉም ይወስዳል” ካሉ በሃላ፤ በአንጻሩ “አንድም አገር ለኢትዮጵያ አንድ ሊትር ውሃ የሚሰጥ አገር የለም ኹሉም ተቀባይ ነው፡፡” ብለዋል፡፡ አክለውም “ግን የእናንተን እንካፈል የእኛን እንዳትጠይቁ ማለት ትክክል አይደለም!” ብለዋል፡፡
“አብረን መኖር ካሰብን፣ ሰላም ካሰብን ከእኛም ከእነሱም ሚዛኑን በጠበቀ መልኩ እየተጋራን መኖር አለብን እንጂ፤ የእኛ ሲሆን ቢወሰድ ችግር የሌለው ከዚያ ሲሆን የማይጠየቅ ከሆነ ፍትሃዊ አይሆንም፤ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ያጣላል” ሲሉም በማብራሪያቸው ተናግረዋል፡፡
በአፍሪካ የሚገኙ 17 አገራት የባህር በር የሌላቸው መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስር ዐቢይ፤ 17ቱ አገራት ኹሉም ተደምረው አንድ ሦስተኛው የሚሆነው የሕዝብ ብዛት ኢትጵያ ውስጥ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ “ወደብ ቢኖረን በኹለት ዓመት ለወደብ በምናወጣው ወጪ ብቻ፣ እንደ ሕዳሴ ግድብ አይነት ትላልቅ ፕሮጀክቶችን መስራት እንችላለን።” ሲሉም በማብራሪያቸው ገልጸዋል፡፡




የህግ ማዕቀፍ ልኖር ይገባል!
በዝህ ዙርያ ሰፋ ያለ አስተያየት ከመሰጠቴ በፍት ግን የህግ ማዕቀፍ መኖሩን ለማረጋገጥ እፈልጋለሁ።