ምክር ቤቱ የዲፕሎማቲክና ሰርቪስ ፓስፖርት ለያዙ ዜጎች ቪዛን ለማስቀረት የሚያግዙ አዋጆችን አጸደቀ

0
164

ማክሰኞ ጥቅምት 6 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባው፤ በኢትዮጵያና በደቡብ ኮሪያ እንዲሁም በህንድ መካከል የዲፕሎማቲክና ሰርቪስ ፓስፖርት ለያዙ ዜጎች ቪዛን ለማስቀረት ያግዛሉ የተባሉ አዋጆችን መርምሮ አጽድቋል፡፡

ስምምነቱ የአገራቱ ዜጎች ለሥራ ጉዳይ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የተሳለጠና ምቹ እንዲሆን ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተጠቅሷል፡፡

በተጨማሪም ምክር ቤቱ በኢትዮጵያና በሊባኖስ መንግሥታት መካከል በሥራ ስምሪት ዘርፍ የተፈረመውን ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ፤ ለዝርዝር እይታ ለሰው ሀብት ልማት ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡

በኢትዮጵያ እና በሩሲያ መካከል በኹለትዮሽ ወታደራዊ ቴክኒካዊ ትብብር ወቅት የተገኙ የአዕምሯዊ የፈጠራ ሥራ ውጤቶችና ንብረቶች የጋራ ጥበቃ ስምምነት ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለውጭ ግንኙነትና ለሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል፡፡

ስምምነቱ የኹለቱን አገራት ወዳጅነት የበለጠ ለማጠናከር የተፈረመ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ በኹለትዮሽ ወታደራዊ የቴክኒካል ትብብር ሂደቱ ውስጥ በአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ መስክ የተሻለ የጋራ መግባባትና ትብብር እንዲኖር ለማድረግ የሚያግዝ ነው ተብሏል፡፡

በተጨማሪም ምክር ቤቱ የአፍሪካ መድሐኒቶች ኤጀንሲ ማቋቋሚያ ስምምነት ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለዝርዝር እይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡

በኢትዮጵያ እና በፓኪስታን መንግሽት መካከል የተደረገ የኹለትዮሽ ንግድ ስምምነትን ለማጽደቅ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡

የንግድ ስምምነቱ ኢትዮጵያ ከፓኪስታን ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነት ለማሳደግ ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር ባሻገር የኢትዮጵያን ንግድ ከቀሪው ዓለም ጋር ለማስተሳሰር እየተደረገ ያለውን ጥረት ከማገዝ አንጻር የጎላ ጠቀሜታ እንደሚኖረው መገለጹን ኤፍ ቢ ሲ ዘግቧል፡፡

በተጨማሪም የምክር ቤቱ 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ስብሰባ ቃለ ጉባዔንም ምክር ቤቱ በስብሰባው መርምሮ አጽድቋል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here