ጣና ፍሎራ በአማራ ክልል ባለው ግጭት ምክንያት ከ600 ሚልየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ወድሞብኛል አለ

ማህበሩ ከ1 ሺሕ በላይ ሠራተኞች የነበሩት ሲሆን አሁን ላይ 100 ቀርተዋል

ማክሰኞ ጥቅምት 6 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በባህር ዳር ከተማ የሚገኘውና ከተቋቋመ 12 ዓመታትን ያስቆጠረው ጣና ፍሎራ የአበባ ልማት ማህበር፤ በአማራ ክልል በፋኖና በመከላከያ ሠራዊት መካከል እየተደረገ ባለው ግጭት ምክንያት ነሀሴ 2/2015 በደረሰበት ጉዳት ከ600 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት እንደወደመበት ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።

የጣና ፍሎራ ምክትል ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ጌታቸው ጨርቆስ፤ የማህበሩ የውሃ ማጠጫ ማሽኖች፣ የኬሚካል መርጫ መሳሪያዎች፣ ማቀዝቀዣዎች፣ ተሸከርካሪዎች፣ ጄኔሬተሮችና ሌሎችም መሳሪዎች እንደወደሙ የገለጹ ሲሆን፤ ንብረቶቹ በአገር ዉስጥ የማይገኙ መሆናቸውንም ተናግረዋል። እንዲሁም የአበባ ማሸጊያ ግብዓቶች እና ማዳበሪያዎችም ጭምር መውደማቸውን አመላክተዋል።

“አሁን ላይ ተቋሙ ምንም አይነት እንቅስቃሴ ለማድረግ የሚችለበት አቋም ላይ አይደለም” ያሉት ጌታቸው፤ “አስተማማኝ ሰላም ስለሌለ ምንም ማድረግ አልቻልንም” ሲሉ ተደምጠዋል።

ከ45 ሄክታር ውስጥ 38 ሄክታር በአበባ ተሸፍኖ እንደነበር የገለጹት ምክትል ሥራ አስኪያጁ፤ “ከእሳት የተረፉው አበባ አሁን ላይ ምግብና ዉሃ እያገኘ አይደለም፡፡” ያሉ ሲሆን፤ የአበቦች በሽታው ደግሞ ሌላ ስጋት መሆኑን ገልጸዋል።

በአበባ እርሻው 18 አይነት የአበባ አይነቶች መኖራቸውን በመግለጽ፤ አሁን ላይ አበቦቹ እየተበላሹ ስለሆነ በድጋሜ ለማልማት ለአንድ አይነት አበባ ከ50 እስከ 70 ሺህ ዶላር እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።

በተመሳሳይም 35 ሄክታር ላይ 13 ሺሕ የአቡካዶ ችግኞች ተተክለው የነበሩ ሲሆን፤ አሁን ላይ ጉዳት እንደደረሰባቸውም ጠቁመዋል።

እንዲሁም 120 ቶን አቡካዶ ወደ ዉጪ ለማልክ ቢታቀድም በክልሉ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት አለመሳካቱን ገልጸው፤ ከጉዳት የተረፉትን ለአገር ዉስጥ ገበያ በኪሳራ እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም በማህበሩ ይሰሩ ከነበሩ 1 ሺሕ በላይ ሠራተኞች ውስጥ አሁን 100 ሲቀሩ ቀሪዎቹ መሰናበታቸው አመላክተዋል።

በመሆኑም “አሁን ላይ ለረጅም ጊዜ አብረውን ሲሰሩ የነበሩ ሠራተኞቻችን ችግር ላይ ወድቀዋል የምንፈልገው ነገሮች ተስተካከለው ወደ ሥራ መመለስ ነው፡፡” ሲሉም ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

አክለውም፤ በክልሉ መንግሥት በኩል ኮሚቴ ተዋቅሮ በባለሙያዎች ጥናቶች እየተደረጉ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ “መንግሥት የራሱን ሀላፊነት ከተወጣ እኛም የድርሻችንን ካደረግን ሥራ ለመጀመር የሚያስችሉ ዕድሎች ይኖራሉ፡፡” በማለት ገልጸዋል።

ጣና ፍሎራ በየዓመቱ በአማካይ 30 ሚሊዮን የአበባ ዘንጎችን በዋናነት ወደ ሆላንድ ይልክ አንደነበርና እስከ 8 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ያገኝ እንደነበርም ጌታቸው አስረድተዋል፡፡

ከኢትዮጵያ የአበባ፣ አትክልት፣ ፍራፍሬ፣ አምራችና ላኪዎች ማኅበር መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በአማራ ክልል የሚገኙ ስድስት የአበባ እርሻዎች በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ ሥራ አቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከቡና ቀጥሎ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የምታገኝበት ምርት የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ሲሆን፣ ዓመታዊ የወጪ ንግድ ገቢው ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር በላይ ደርሷል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here