ረቡዕ ጥቅምት 7 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) አፍሪካ አሁን አቅም እና ችሎታዋን እየተገነዘበች ትገኛለች ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በቻይና ቤጂንግ በተካሄደው በ3ኛው የቤልት ኤንድ ሮድ ፎረም መክፈቻ መርሃ ግብር ላይ ንግግር አድርገዋል፡፡
በመክፈቻ ንግግራቸውም አፍሪካ አሁን አቅም እና ችሎታዋን እየተገነዘበች እንደምትገኝ ገልጸው፤ “ከዚህ ቀደም በጎን የተሰለፈችው አህጉር የስነ ሕዝብ አወቃቀር ክፍፍል እና የተፈጥሮ ሀብቷን በመጠቀም ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ሃይል ማመንጫ ሆናለች” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የአፍሪካ አህጉር በተለይ በአየር ንብረት ቀውስ እና በሌሎች የአለም ክፍሎች ግጭት መዘዝን ማስተናገዷን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “አሁን ላይ የጋራ ደህንነትን በሚነኩ መድረኮች ታዛቢ ብቻ መሆን አንችልም” ሲሉም ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመድረኩ፤ የቻይና-አፍሪካን ግንኙነት ጥንተ መሰረት እና እድገት አውስተው በቢአርአይ የመሰረተ ልማት ክንውን በአፍሪካ አህጉር የተጣለውን ጠንካራ የትብብር መሰረት አንስተዋል፡፡
በዚህም በማደግ ላይ ያለውን የአፍሪካን ተፅእኖ የመፍጠር አቅም አፅንዖት በመስጠት፤ በባለብዙ ወገን መድረኮች አካታችነትን ማረጋገጥ ተገቢ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በቻይና ይፋዊ ጉብኝት ሲያደርጉ ከአራት ዓመት በኃላ ይህ የመጀመሪያቸው ሲሆን፤ በ3ኛው የቤልት ኤንድ ሮድ አለም ዓቀፍ ትብብር መድረክ ላይም በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡



