ረቡዕ ጥቅምት 7 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በጅግጅጋ ከተማ ታይዋን የገበያ ማእከል በደረሰው የእሳት አደጋ ንብረታቸው ለወደመባቸው ወገኖች ለ2ተኛ ዙር ከ100 ሚሊየን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ ተደርጓል።
ድጋፉ በገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴው ከተለያዩ አካላት የተሰበሰበ ሲሆን፤ ለ339 ተጎጂዎች በተቋቋመው ኮሚቴ በኩል እንደወደመባቸው ንብረት ሁኔታ በመደልደል ነው 100 ሚሊየን 872 ሺሕ 497 እንዲከፋፈል የተደረገው።
በሥነ ስርዓቱ ላይ በመጀሪያው ዙር ድጋፍ በእሳት አደጋው የደረሰባቸው ውድመት ከ100 ሺህ ብር በታች ለሆኑ ግለሰቦች ሙሉ በሙሉ ክፍያ የተፈጸመላቸው መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ 2ተኛው ዙር ደጋፍ እንደ ወደመባቸው ንብረት ከ10 በመቶ እስከ 50 በመቶ ድጋፍ እንዲደርሳቸው ተደርጓል ተብሏል።
በሥነ ስርዓቱ ላይ በአሜሪካ፣ ኖርዌይና ደቡብ ሱዳን የሚኖሩ የክልሉ ተወላጅ ዲያስፖራ ተወካዮችና የእሳት አደጋው ተጎጂ ወገኖች ተገኝተዋል።
በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ሰኔ 30/ 2015 ሌሊት በተከሰተው የእሳት አደጋ 932 የንግድ ሱቆች መውደማቸው የሚታወስ ሲሆን፤ በዚህም ከ1.5 ቢሊየን ብር በላይ የሚሆን ንብረት ውድመት ደርሶበታል።



