በአርጎባ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳ 17 ሺሕ የሚሆኑ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ተባለ

0
148

አርብ ጥቅምት 9 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በአርጎባ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳ በመኸር የተዘራው ሰብል በዝናብ እጥረት ምክንያት ምርት አልባ መሆኑን ተከትሎ፤ 17 ሺሕ የሚሆኑ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ተገልጿል፡፡

በዚህም በወረዳው ስድስት ቀበሌዎች በድርቅ ምክንያት ሙሉ በሙሉ ምርት አልባ መሆናቸው የተነገረ ሲሆን፤ የወረዳው አርሶ አደሮችም መንግሥት አስቸኳይ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል፡፡

አርሶ አደሮቹ ባለፈው ዓመት ከመኸር እርሻ የተሻለ ምርት ማግኘታቸውን ገልጸው፤ ዘንድሮ ግን በዝናብ እጥረት ምክንያት የዘሩት ዘር ሙሉ በሙሉ ምርት አልባ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በፊት እንዲህ አይነት የከፋ ድርቅ ተከስቶ እንደማያውቅ የገለጹት አርሶ አደሮቹ፤ ቤተሰባቸውን ለመመገብ እንሰሳትን በእርካሽ ለመሸጥ ቢሞክሩም፣ ችግሩ የኹሉም በመሆኑ ገዥ መጥፋቱን አስረድተዋል።

“በዓመት አንዴ ብቻ በመኸር ስለምናመርት በዝናብ እጥረት ምክንያት የዘራነው በመድረቁ እኛም እንስሳቶቻችንም ለረሀብ አደጋ ተጋልጠናልና፤ የመንግሥትን ድጋፍ እንሻለን” ብለዋል።

የአርጎባ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አደም እንድሪስ፤ በ2015/16 የመኸር እርሻ ከ6 ሺሕ 900 ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ተሸፍኖ እንደነበር ገልጸው፤ ከዚህም ከ157 ሺሕ ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቅ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ነገር ግን በድርቅ ምክንያት ከ3 ሺሕ 800 ሄክታር በላይ ወይም 54 በመቶ ማሳ ሙሉ በሙሉ ምርት አልባ ሆኗል ብለዋል።

በወረዳው ዘጠኙም ቀበሌዎች ድርቁ ጉዳት ማስከተሉን የገለጹም ሲሆን፤ ስድስት ቀበሌዎች መሉ በሙሉ ምርት የማያገኙበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን አስረድተዋል፡፡

አያይዘውም በዚህ ሳቢያ በወረዳው በአጠቃላይ 35 ሺህ ነዋሪዎች ድጋፍ ያሉ ሲሆን፤ 17 ሺሕ የሚሆኑት ዜጎች ደግሞ አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ የሚፈልጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የተወሰኑ አካባቢዎች ብዙም እርጥበት የማይፈልጉ እንደ ሽምብራ ያሉ ሰብሎችን ለመዝራት ሙከራ ማድረጋቸውን የገለጹት ኀላፊው፤ የመስኖ አቅምን ማጎልበት ችግሮችን ለመቋቋም እንደሚያግዝ መናገራቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡

ኀላፊው አክለውም የዞን፣ የክልል እና የፌዴራል የሚመለከታቸው አካላትና መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች ለተከሰተው ድርቅ ትኩረት እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በአርጎባ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳ ዘጠኝ ቀበሌዎች በዋናነት ማሽላ፣ ጤፍ፣ ማሾ፣ በቆሎ እና ሰሊጥ ይመረታል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here