በትግራይ ክልል ከ30 ሺሕ በላይ ሕጻናት ከቤተሰቦቻቸው ተለያይተዋል ተባለ

በክልሉ ወደ ጎዳና የሚወጡ ሕጻናት ቁጥር በከፍተኛ ኹኔታ ጨምሯል

0
170

ቅዳሜ ጥቅምት 10 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በትግራይ ክልል ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተያያዘ ከ30 ሺህ በላይ ሕጻናት ከቤተሰቦቻቸው ተለያይተው በችግር ውስጥ እንደሚገኙ፤ የክልሉ ሴቶች ሕጻናት እና ወጣቶች ቢሮ ለአዲስ ማለዳ ገልጿል፡፡

በቢሮው የሕጻናት አገልግሎት ኢኒስፔክሽን ባለሙያ የሆኑት ዳዊት ጌታቸው በክልሉ በጦርነቱ ወቅት በተለያዩ ምክንያቶች ከቤተሰቦቻቸው የተለያዩ በርካታ ሕጻናቶች መኖራቸውን ገልጸው፤ ሕጻናቱ “ከቤተሰቦችን ጋር አገኛኙን” በማለት ቢሮውን በመጠየቅ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

በዚህም “እስካሁን ከ3 ሺሕ 800 በላይ ሕጻናትን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ማገናኘት ተችሏል” ያሉት ባለሙያው፤ “ነገር ግን አሁን ላይ በክልሉ ከ30 ሺሕ በላይ ሕጻናት ከቤተሰቦቻቸው ተለያይተው በችግር ውስጥ እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በመቀሌ ብቻ ከ15 ሺሕ በላይ ሕጻናት ከቤተሰቦቻችው ተለያይተው እንደሚገኙም የገለጹት ዳዊት፤ ሕጻናቱ በምግብ እጥረት ችግር ለሞትና ለከፍተኛ ጉዳት እየተዳረጉ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ዳዊት አክለውም፤ መቀሌን ጨምሮ በክልሉ ዋና ዋና ከተሞች ላይ በርካታ ሕጻናት በየጎዳናው ወጥተው እንደሚታዩ የገለጹ ሲሆን፤ በጦርነቱ ቤተሰባቸውን ያጡ፣ ቤተሰብ ኖሯቸው በቂ ምግብ ማግኘት ያልቻሉ በተለያዩ ምክንያት ለችግር ተጋልጠው መፍትሄ ለማግኘት ወደ ጎዳና የወጡ ሕጻናት ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን አስረድተዋል፡፡

“ሕጻናቱን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለማገናኘት ጥረት እየተደረገ ነው ከዚህ በፊትም ያገናኘናቸው ሕጻናት አሉ፡፡” ያሉም ሲሆን፤ “ወደ ቤተሰቦቻቸው ለመመለስ የሚፈልጉና ለመመለስ የሚችሉትን ለመመለስ፤ የማይችሉትን ደግሞ አማራጭ ቤተሰብን በማፈላለግ ከእነርሱ ጋር እንዲገናኙ ለማድረግ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በክልሉ በአደጋ ጊዜ ሕጻናትን ከአደጋ ለመጠበቅ የተደራጁ 11 ክላስተሮች መኖራቸውን በማንሳትም፤ እነዚህ አደረጃጀቶች ሥራቸውን በአግባቡ ለማከናወን የበጀትና ሌሎች መሰረታዊ ችግሮች ፈተና እንደሆኑባቸው ገልጸዋል፡፡

የፌደራል መንግሥቱ በሰኔ ወር 2015 ላይ በጦርነቱ ሥነ ልቦናዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳት የደረሰባቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ማገገም በሚችሉበት አሰራር ዙሪያ ለቢሮው ጥቂት ሠራተኞች ስልጠና መስጠቱን ያስታወሱት ባለሙያው፤ “ስልጠናው እስከ ወረዳ ድረስ አውርደን ለኹሉም ባለሙያዎች እንሰጣለን ቢባልም፤ እስካሁን አልተሰጠም።” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ከኹለት ዓመታት በላይ በፌዴራል መንግሥት እና በሕወሓት ኃይሎች መካከል ሲደረግ የነበረው ውጊያ ካስከተለው ቀውስ ጋር ተያይዞ፤ በተለያዩ በሽታዎች እንዲሁሜ በረሃብ የሚሞቱ እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት እና እናቶች ቁጥር በየዕለቱ እየጨመረ መምጣቱን የክልሉ ጤና ቢሮ ማስታወቁ ይታወሳል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here