ሰኞ ጥቅምት 12 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በአማራ ክልል መንግሥት የህግ ማስከበር ዘመቻ ጀምሪያለሁ ካለበት ጊዜ ጀምሮ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች በመከላከያ ሰራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተደረገ ባለው ውጊያ ታጣቂዎች፤ በሴቶች ላይ የሚደርሱት የአስገድዶ መድፈር ጥቃት በስፋት እየተስተዋለ መሆኑን የሆስፒታል ሃላፊዎች እና የጥቃቱ ሰለባዎች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
ለደሕንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈልጉ የደብረማርቆስ ሰፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሐኪም፤ በምስራቅ ጎጃም ዞን ዋና ከተማ ደብረማረቆስ ከነሐሴ 19/2015 እስከ ሠኞ ነሐሴ 22/2015 ድረስ እየተካሄደ በነበረው ግጭት ምክንያት፤ ምሽት አካባቢ ሴቶች ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱ በከተማዋ በሚገኙ ታጣቂዎቸ የአስገድዶ መደፈር ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታል የመጡ በርካቶች ናቸው ብለዋል፡፡
ነሐሴ 21/2015 ምሽት አስራ ኹለት ሰዓት አካባቢ በአንድ ምሽት ብቻ በከተማው የሚኖሩ ኹለት ሴቶች የአስገድዶ መደፈር ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታል መጥተዋል ነው ያሉት፡፡
የአስገድዶ መደፈር ከደረሰባቸው ወጣቶች መካከል አዲስ ማለዳ አንዷን አነጋግራለች፡፡ አወቀች (ለደህንነቷ ሲባል ሥሟ የተቀየረ) ትባላለች። የተወለደችው በምስራቅ ጎጃም ዞን ወስጥ በምትገኝ ትንሽ መንደር ውስጥ ሲሆን፤ በልጅነቷ እናቷ በመሞታቸው ከታላቅ እህቷ ጋር ማደጓን ትናገራለች፡፡ ከእህቷ ጋር በምታድግበት ወቅት ለአቅመ ሄዋን ስትደርስ አንድ ወጣት ካላገባሁሽ እያለ ያስቸግራት ነበር፡፡
እሷም ትዳር ከመሰረተች እህቷ ጋር ተደርባ በመቀመጧ ስለከበዳት አግብታ ራሷን መቻልን አሰበችና ሲያስቸግራት የነበረውን ወጣት አግብታ በደብረማርቆስ ከተማ መኖር ጀመሩ፡፡
አበበችም ወጣትነቷን አጣጥማ ሳትጨርስ የኹለት ልጆች እናት ሆነች፡፡ ኹለት ልጆችን ከወለደች በኋላ ልጆቹ በሥነ ስርዓት ሳያድጉ ባለቤቷ አልፈልግሽም ብሎ ልጆቹን አሳቅፏት ጠፋ፡፡
አበበች ከባለቤቷ ጋር ከተለያየች በኋላ በደብረማርቆስ ከተማ በነዋሪዎች ቤት እየዞረች እንጀራ እየጋገረችና ልብስ እያጠበች ልጆቿን ማሳደጉን ተያያዘችው፡፡
በዚህ ወቅት ልጆቿ የአራት እና የ10 አመት ሕጻናቶች ናቸው፡፡ በአማራ ክልል በመከላከያ ሰራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተደረገ ባለው ውጊያ ታዲያ የኹለት ልጆች እናት የሆነችው አበበች ልጆቿን አብልታ ለማደር ስትል በደብረማርቆስ እየተደረገ የነበረውን የተኩስ ልውውጥ ወደ ጎን ትታ በጨለማ እንጀራ ልትጋገር ወደ ሌላ ሰፈር አቀናች፡፡
እንጀራውን ቶሎ ጋግራ የተከፈላትን ብር ይዛ ልጆቿን ምግብ ለማብላትወደ ተከራየቻት ትንሽዬ ቤቷ በምትሄድበት ወቅት “እንዳትንቀሳቀሽ ቁሚ” የሚል ድምጽ ከወደኋላዋ ስትሰማ ባለችበት መቆሟን ትናገራለች።
ዘወር ስል ፊታቸውን በጭምብል የሸፈኑ ኹለት የጦር መሳሪያ የታጠቁ ሰዎች መሳሪያቸውን እሷ ላይ ደግነው፤ “ወደ ምንጠቁምሽ ቦታ ሂጅ ካለሆነ እዚሁ ላይ እንገልሻለን” እንዳሏት ትናገራለች፡፡
ሕጻን ልጆቿ ከተከራየችው ቤት ያለምንም ጠባቂ ትታ የወጣችው አወቀች፤ ህፃኖቹም “እናታችን ትመጣለች፤ ምግብም እንበላለን” እያሉ እየጠበቁ ባለበት ወቅት እናታቸው ጭንብል በለበሱ የታጠቁ ሃይሎች ተይዛለች፡፡
ወጣቷ በኹለት ታጣቂዎች ተይዛ እነሱ ወዳዘዝዋት ቦታ እየወሰዷት እያለ ሌላ የ16 ዓመት ሕጻን ልጅ መንገድ ላይ ሲያገኟት እሷንም እንደሚገሏት እያስፈራሩ በከተማው በሚገኜው ዶኬ የተሰኘ ክሊኒክ አቅራቢያ በሚገኝ ቦታ በመውሰድ ጾታዊ ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ነግራናለች፡፡
ኹለቱም ሴቶች ላይ ጾታዊ ጥቃት የፈጸሙ ታጣቂዎች ሁለት ናቸው። ታጣቂዎቹ ማን እንደሆኑ መለየት አልቻልንም ያለችው የኹለት ዓመት ሕጻኖች እናት፤ ታጣቂዎቹ ጾታዊ ጥቃት ከፈጸሙ በኋላም ሊለቋቸው እንዳልቻሉ እና ሌሊቱን ሙሉ አብረዋቸው እንዲያድሩ ማድረጋቸውን ትናገራለች።
ከፆታዊ ጥቃቱ በኋላ ወደ ልጆቿ ስትሄድ፤ ምግብ ባለመብላታቸው፣ በማልቀሳቸው እና ምንም አይነት እንቅልፍ ሳይተኙ በማደራቸው ለሕመም እንደተጋለጡባት ገልጻለች፡፡
አወቅች እና ሌላኛዋ የጾታዊ ጥቃት ሰለባ የሆነችው ወጣት በዚህ ወቅት በደብረማርቆስ ሆስፒታል የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ተገልጿል።
በክልሉ እየተደረገ ያለው ውጊያ በአስቸኳይ እንዲቆምና ጾታዊ ጥቃት ፈጻሚዎችም ለሕግ እንዲቀርቡልን ስትል አወቀች ትማጸናለች።
አወቀች በዚህ ወቅት በከፍተኛ ችግር ውስጥ ትገኛለች። እሷም ልጆቿም ለከፍተኛ ሕመም ተጋልጠዋል። እሷ በመታመሟ ስራ መስራት ባለመቻሏ ለልጆቿ ምግብ መመገብ እንዳልቻለችና በከፍተኛ ችግር ውስጥ መሆኗን ነግራናለች።
ሌላኛዋ የአስገድዶ መድፈር የተፈጸመባትን ወጣት ለማነጋገር ሙከራ ብናደርግም፤ ፈቃደኛ ሳትሆን በመቅረቷ እና የአዕምሮ ሕመም ችግር ስላጋጠማት ከሆስፒታል እወጣለሁ በሚል እያስቸገረች ትገኛለች።
የደብረማርቆስ ሰፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሃኪም በበኩላቸው የአስገድዶ መደፈር ከተፈጸመባቸው በኋላ ወደ ሆስፒታል መጥተዋል ብለዋል፡፡
ጾታዊ ጥቃት ከተፈጸመባቸው ሴቶች መካከል አንዷ ሕጻን መሆኗን ተከትሎ ለሕክምና ወደ ሆስፒታል ከመጣች በኋላ የአዕምሮ ዕክል ገጥሟት ከሆስፒታል አምልጣን ወጥታ ጠፍታብናለች ሲሉ አክለዋል፡፡
የአማራ ክልል ሴቶች ሕጻናት እና ማህበራዊ ጉዳይ የሴቶች ግንዛቤ ንቅናቄ ማስፋፊያ ባለሙያ የሆኑት ሳድያ ኡስማን በ2014 እና 2015 የሰሜኑን ጦርነት ጨምሮ 2980 የሚሆኑ ሴቶች እና ሕጻናት ጾታዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡
የሰሜኑ ጦርነት ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ እስከ 2016 መስከረም ወር ድረስ ከሦስት ሺሕ ስድስት መቶ በላይ ጾታዊ ጥቃት መድረሱን የክልሉ ሴቶችና ሕጻናት ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታውቋል።
በክልሉ በመከላከያ ሰራዊትና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተደረገ ያለው ውጊያ በአስቸኳይ ካልቆመ በሴቶች ላይ እየደረሰ ያለው ጾታዊ ጥቃት እየተባባስ መሆኑና ላልተፈለገ እርግዝና እና ተላላፊ በሽታዎች እየተዳረጉ መሆኑን ቢሮው አሳስቧል።



