ረቡዕ ጥቅምት 14 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት እና አለቃቀቅ ደንቦችና መመሪያዎች ዙሪያ በኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን መካከል ለኹለት ቀናት በግብጽ መዲና ካይሮ ሲካሄድ የነበረው ሦስተኛው ዙር የሦስትዮሽ ድርድር ትናንት ማምሻውን ተጠናቋል፡፡
በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር እና በህዳሴው ግድብ የኢትዮጵያ የባለሙያዎች ቡድን መሪ አምባሳደር ስለሺ በቀለ፤ “ድርድሩ መጠነኛ መሻሻልና መግባባት የታየበት ነበር” ሲሉ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት አስታውቋል፡፡
ቀጣዩን ድርድር በታህሳስ ወር ውስጥ በኢትዮጵያ አዲስ አበባ ለመቀጠል ስምምነት መደረጉን ገልጸዋል፡፡
አምባሳደር ስለሺ “ኢትዮጵያ የዓባይን ወንዝ ፍትሃዊና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ የመጠቀም መርህ ላይ በመመሥረት ኹሉም አሸናፊ የሚሆንበት ውጤት ላይ ለመድረስ ቁርጠኛ አቋም አላት” ሲሉም ገልጸዋል፡፡



