ረቡዕ ጥቅምት 14 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ “ከዕዳ ወደ ምንዳ – ታላቁ ትርክት” በሚል ርዕስ ለፓርቲው ከፍተኛ አመራሮችና አባላት ንግግር ባደረጉበት ወቅት ግጭት የብልፅግና መንግሥት ዋነኛ አጀንዳ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ብልጽግና የሚሰራቸውን ሥራዎች “ሊያንኳስሱ” እና “ሊያዛቡ” የሚችሉ ወገኖች ቢኖሩም፤ ገዢው ፓርቲ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር በሚያደርገው ጥረት “የሚያቆመው ኃይል የለም” ብለዋል፡፡
እንዲሁም “ግጭት አለ፣ አላስፈላጊ መገዳደል አለ፣ ግን መከላከያና ፖሊስ እየተቆጣጠረው ነው፡፡ የምታርስ እረስ፣ የምትነግድ ነግድ፣ ኢንዱስትሪም አስፋፋ፣ የፓርቲውና መንግሥት ዋነኛ አጀንዳ አድርገህ፣ የሥራህን ድካም በእሱ መሸፈን አታስብ” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
“ኢትዮጵያ ውስጥ እርስ በእርስ መበላላት፣ መጠላላት፣ መገፋፋት መፈናቀል፣ መቆም አለበት አደገኛ ነገር ነው” ሲሉ የገለጹም ሲሆን፤ “ከዚያ በላይ እንዳንወነጨፍ እያደረገን ነው፤ ግን ኹሉም አጀንዳ እሱ ብቻ አይደለም” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው “ኢትዮጵያ ውስጥ አብሮ ከመኖር ውጪ አማራጭ የለም። ማጥፋት መጨፍለቅ አይቻልም” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
“በየቀኑ የምንዘራቸው የውሸት ወሬዎች ያስተሳሰረንን የገመደንን አንድ የሚያደርገንን ነገር የሚያላላ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “እያንዳንዱ ብሔር የእያንዳንዱ እምነት ተከታይ ማንም ኢትዮጵያዊ፤ የጋራ የሆነ አሰባሳቢ አጀንዳ ቢፈጥርና በዛ ልክ ቢመላለስ የሚጠቀመው እራሱና ልጆቹ ናቸው፡፡” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
“ኦሮሞና አማራ ተስማምተህ በሰላም ከመኖር ውጪ አማራጭ የለም፤ ለራስህ ስትል በሰላም ኑር፣ ብታሸንፍ ችግር አልነበረውም ግን አትችልም። ትግራይና ጉራጌ፣ ጉራጌና ስልጤ ኹላችሁም በሰላም፣ በትብብር መኖር ብቻ ነው የሚሳድገን። ከዚህ ውጪ ያለው ሊገድል ይችላል ግን ድል አያመጣም” ሲሉም ተናግረዋል።
አክለውም “አማራ ሆይ! ኦሮሞ ሆይ! ሥማ እዚህ አገር ውስጥ ያንጋቶምን ወቅጠህ መኖር አትችልም! ትንሹንም ቢሆን አክብረህ እና አቅፈህ በመኖር ብቻ ነው የበለጸገች ኢትዮጵያን የምታረጋግጠው፡፡ ያንተ ቁጥር ትዋጋበት ይሆናል እንጂ የጸናችና የበለጸገች ኢትዮጵያን አያመጣልህም” ብለዋል፡፡
“ጥምቅት መጣ በሰላም ያልፍ ይሆናል?፣ ኢሬቻ መጣ በሰላም ያልፍ ይሆናል?፣ እንዴት ሰው ያን የሚያህል ሰው የሚያሳባስብ በዓል እንዴት የጭንቅት ምንጭ ይሆንለታል? አንተ ተጨንቀህስ እንዴት ነው ሰው ከውጪ መጥቶ የሚያይልህ?” ሲሉም አመራሮቹን ጠይቀዋል። ሰለሆነም ይህን ሰላማዊ ነገር በውስጣችን መገንባት ያስፈልጋል፡፡” ሲሉ አሳስበዋል፡፡
አክለውም “የሰከሩ ያበዱ ሰዎች በትርክት የሚያሳብዷት ኢትዮጵያን ለመፍጠር ሲያስቡ ተባባሪ አትሁኑ” ብለዋል።
ለዚህ አላማ ተባባሪ መሆን የሚፈልጉ “እዚህ ዉስጥ ብዙ አለ አትቀመጥ እዚህ ጊዜህን አታባክን፣ ብዙ አለ ጊዜ የሚያባክን እዚህ ውስጥ፣ ቦታህን ፈልግ ጊዜህን ተጠቀምበት” ሲሉም ለአመራሮቹ አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ የብልጽግና ፓርቲ ተወካዮችን ከመምረጥ ባሻገር፤ በተለያየ ወቅት ለሚቀርብለት ጥሪ በጎ ምላሽ እየሰጠ እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
“ከዕዳ ወደ ምንዳ” በሚል መሪ ሀሳብ በ10 ከተሞች 12 ሺሕ ለሚሆኑ የብልፅግና ፓርቲ አመራሮች ለ11 ቀናት ስልጠና ሲሰጥ መቆየቱ ይታወቃል፡፡



