የአዳዲስ ሆቴሎች የኮከብነት ደረጃ ውጤት በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግ ተገለጸ

0
150

ሐሙስ ጥቅምት 15 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በአገር ደረጃ ከ2014 ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው የአዳዲስ ሆቴሎች የኮከብነት ደረጃ ውጤት፤ በሳይንስ ሙዚየም በተዘጋጀው አገር አቀፍ የቱሪዝም ኤግዚቢሽንና ሆስፒታሊቲ ማጠናቀቂያ ላይ ይፋ እንደሚደረግ የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታውቋል።

መስፈርቱን ያሟሉ 20 ለሚሆኑ ሆቴሎች የኮኮብነት ደረጃ እንደሚሰጣቸው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ገልጿል።

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ሆቴሎችና ሎጆች የኮከብነት ደረጃ ከተመደበ ከብዙ ዓመታት በላይ ሆኗቸዋል ያሉ ሲሆን፤ የሆቴሎች የደረጃ ምደባ መስጠት አስፈላጊ መሆኑንም አንስተዋል።

ይህም ለሆቴሎች አሁን ባላቸው የብቃትና የጥራት ደረጃ ልክ የኮኮብነት ደረጃ መስጠት በቱሪዝም ገበያ ልማቱ ላይ አወንታዊ ተፅዕኖ እንዳለው ተናግረዋል።

በሚኒስትሩ የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ብቃት ማረጋገጥና ደረጃ ምደባ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አታሪኩ ደምሴ በበኩላቸው ከ2014 ጀምሮ ምደባ ሲካሄድ የቆየው የሆቴሎች የኮከብነት ደረጃ በኤግዚቢሽኑ ማጠናቀቂያ ላይ ይፋ እንደሚደረግ ገልጸው፤ በዚህም 20 ሆቴሎች መስፈርቱን አሟልተዋል ብለዋል።

147 ሆቴሎች ተለይተው በኹለት ዙር የደረጃ ምደባ ተደርጓል ያሉት መሪ ሥራ አስፈጻሚው፤ በመጀመሪያው ዙር በተቀመጠው መስፈርት መሠረት ማሟላት ያለባቸውን እንዲያሟሉ ሙያዊ ድጋፍ መደረጉን ጠቁመዋል።

በምደባውም አዳዲስ መመሪያዎች መካተታቸውንም በመግለጽ፤ በተለይ የእሳት አደጋ መቆጣጠሪያ ከማሟላት አንጻር ትኩረት መደረጉን ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት ከነበረው አመዳደብ በተሻለ መልኩ የደረጃ ምደባ ቴክኒክ ኮሚቴ ተዋቅሮ ሲሠራ እንደ ነበርም ተናግረዋል።

የነበሩ ውስንነቶች ተቀርፈው ሥራው በጥራት እንዲሠራ አስፈላጊውን ቁጥጥር ተደርጓል ያሉት ታሪኩ፤ በተጨማሪም መዛኝ ባለሙያዎች ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲመዝኑ ክትትል አድርገናል ብለዋል።

የሆቴል ባለቤቶች ለማስመዘን ያላቸው ፍላጎት አነስተኛ በመሆኑ ሥራው ለዓመታት እንዲጓተት እንዳደረገውም ታሪኩ መናገራቸውን ኢፕድ ዘግቧል።

በአሠራሩ መሠረት በየሦስት ዓመቱ ውጤት ምደባ መደረግ ያለበት ሲሆን፤ በተያዘው ዓመት የነባር ሆቴሎች ዳግም ምደባ በቅርቡ ለመጀመር ቅድመ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸው ተነግሯል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here