ሐሙስ ጥቅምት 15 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) ዳሸን ባንክ በ2015 በጀት ዓመት ከግብር በፊት 5 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱን ያስታወቀ ሲሆን፤ ይህም ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ31 ነጥብ 9 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን ገልጿል፡፡
የባንኩ ባለአክሲዮኖች 30ኛ መደበኛ ጉባኤ በዛሬው ዕለት ተካሂዷል፡፡

በጉባዔውም የዳሸን ባንክ የቦርድ ሊቀመንበር ዱላ መኮንን፤ ባንኩ ከግብር በፊት 5 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱን የገለጹ ሲሆን፤ በበጀት ዓመቱ 18 ቢሊዮን ብር ገቢ ማስመዝገቡንም ተናግረዋል፡፡
ሊቀመንበሩ አክለውም ባንኩ ተጨማሪ 23 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ መሰብሰብ መቻሉን በማንሳት፤ ይህም የባንኩን ተቀማጭ 114 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር እንዳደረሰው ገልጸዋል፡፡
በዚህም የባንኩ አጠቃላይ ሀብት 144 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር መድረሱን አስረድተዋል፡፡
የቦርድ ሊቀመንበሩ በባንኩ ዘርፍ ባለፈው በጀት ዓመት በርካታ አዳዲስ መመሪያዎች እንደወጡና የነበሩ መመሪያዎችም ማሻሻያ እንደተደረገባቸው የገለጹ ሲሆን፤ እነዚህ መመሪያዎችም በባንኮች የሀብት መጠን፣ የሥራ ማስኬጃና ተያያዥ ወጪዎችና ትርፋማነት ላይ የራሳቸው ተፅዕኖ እንደነበራቸው አብራርተዋል፡፡
በተጨማሪም እያደገ የመጣው የዲጂታል መሰረተ ልማት ለረጅም ጊዜ በባንኮች ብቻ ይሰጡ የነበሩ አገልግሎቶች ከባንኮች ውጭ እንዲሰጡ እድል መፍጠሩንና ያነሱ ሲሆን፤ ይህም ለባንኮች ጭምር ሰፊ እድል እንዲፈጠር ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

የዳሽን ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አስፋው ዓለሙ በበኩላቸው፤ ያለፈው ዓመት ባንኩ ተደራሽነቱን ይበልጥ ከማስፍት አንጻር አዳዲስ ደንበኞችን ከማምጣትና ሀብት ከማሰባሰብ አኳያ አውንታዊ ውጤቶችን ያስመዘበበት ዓመት እንደነበር ጠቁመዋል፡፡
ባንኩ ባለፈው በጀት ዓመቱ 253 አዳዲስ ቅርንጫፎችን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች መክፈቱንና አጠቃላይ የቅርንጫፎቹን ብዛት ከ835 በላይ መድረሳቸውን አስረድተዋል።
ባንኩ ከ5.2 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች እንዳሉትም በማንሳት፤ የደንበኞቹን ፍላጎት የሚመጥኑ የባንክ አገልግሎቶችን መስጠቱን እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
ዳሸን ባንክ ባለፈው በጀት ዓመት ማሕበራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት ከ285 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ ማድረጉንም ገልጸዋል
የዳሸን ባንክ አጠቃላይ ካፒታሉ 19 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር፤ የተከፈለ ካፒታሉ ደግሞ 9 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር መድረሱም በጉባዔው ተነግሯል።



