ረቡዕ ጥቅምት 21 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በኢትዮጵያ የቴሌኮም አገልግሎት እንዲሰጥ ፍቃድ ያገኘው አለም ዓቀፍ የቴሌኮሙኒኬሽን ኩባንያ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ፤ በሚቀጥሉት ሳምንታት በትግራይ ክልል የኔትወርክ እና የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ለማካሄድ በሚያስችለውን ውይይት ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር አድርጓል፡፡
በሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዊም ቫንሔለፑት የተመራው ልዑካን ቡድን በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ እና በክልል ካቢኔ የመሠረት ልማት ጉዳዮች ኃላፊ የዓለም ፀጋይ ጋር ባለፈው ሳምንት ተወያይቷል፡፡
በውይይቱም በክልሉ የኔትወርክ እና መሠረት ልማት ዝርጋታ በሚቀጥሉት ሳምንታት ውስጥ ስለማስጀመር ማቀዱን አስታውቋል።
የኩባንያው ልዑካ ቡድን ከትግራይ ክልል በተጨማሪም በሶማሌ፣ ሐረር ከልሎችን እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ጉብኝት አድርጓል።
ጉብኝቱ ከከፍተኛ የክልል አመራሮች ጋር ለመገናኘት፣ የገበያ እና የኔትወርክ ዝርጋታ የመስክ ጉብኝት ለማካሔድ የታቀደ መሆኑን ሳፋሪኮም አስታውቋል።



