ረቡዕ ጥቅምት 21 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) ባለፈው ሳምንት በድሬደዋ መካነ እየሱስ ቤተክርስቲያን እና በከተማ ከንቲባ ጽ/ቤቱ መካከል ተፈጥሮ የነበረው ችግር በውይይት መፈታቱን ቤተክርስቲያኗ አስታውቃለች፡፡
“ቤተክርስቲያኗ ትፍረስ” በሚል ላወጣው ደብዳቤም የከንቲባ ጸ/ቤቱ ቤተክርስቲያኗን ይቅርታ መጠየቁን እና ኹሉም ነገር በንግግር እንደሚፈታ መናገሩን ገልጻለች፡፡
በተደረገው ንግግርም ቤተክርስቲኗ የያዘችውን ይዞታ ማልማት ከቻለች በቦታው እንድትቀጥል ካልሆነ ግን የከንቲባ ጸ/ቤቱ ተለዋጭ ቦታ ላይ የምትክ ቤት ሰርቶ እንደሚሰጥ ቃል መግባቱን የቤተክርስቲያኗ ሰብሳቢ በለሳቸው አምባሮ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ራዲዮ ጣቢያ ተናግረዋል፡፡
ከቦታው ተነስቶ ወደ ተለዋጭ ቦታ መሄዱም ቢሆን ከቤተክርስቲያኗ መሪዎች ጋር በመነጋገር ብቻ እንደሆነ መተማመን ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡
ቀደም ሲል የተላከው ደብዳቤም ቤተክርስቲያነኗ ዙሪያ ላይ ላሉ ተቋማት የተዘጋጀ መሆኑን ከንቲባው መናገራቸውን የገለጹት የቤተክርስቲኗ ሰብሳቢ፤ ይቅርታ መጠየቃቸውንም አነስተዋል፡፡
ስለሆነም ከተቀመጡት ኹለት አማራጮች መካከል ቤተክርስቲያኗ የፈለገችውን መምረጥ እንደምትችል የከንቲባ ጸ/ቤቱ ገልጿል፡፡
በሚቀጥለው ሰኞ ከድሬደዋ ከንቲባ ጋር ለመነጋገር ዋናው ሲኖዶስ ከአዲስ አበባ ወደ ድሬደዋ እንደሚያመራ የተገለጸ ሲሆን፤ ከሚደረገው ሰፊ ውይይት በኋላ ቤተክርስቲያኗ የሚበጃትን ትምርጣለች ብለዋል፡፡
በመጨረሻም የከተማ ከንቲባ ጽ/ቤቱ ጥፋቱን አምኖ ይቅርታ መጠየቅ በመቻሉ ቤተክርስቲያኗ በጣም እንደምታመሰግን የቤተክርስቲያኗ ሰብሳቢ በላቸው አምባሮ አስታውቀዋል፡፡
የድሬደዋ መካነ እየሱስ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን ለ40 ዓመታት ያገለገለችበትንና የሕጋዊነት ይዞታ ማረጋገጫ ካርታ የያዘችበትን ቦታ፤ የከተማዋ ከንቲባ ጽ/ቤት “ቦታው ለሆቴል ቱሪዝም በማስፈለጉ በአንድ ወር ውስጥ ከቦታው እንድትነሳ” ለቤተክርስቲያኗ ደብዳቤ መላኩ መዘገቡ ይታወሳል፡፡



