49 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በኬንያ በቁጥጥር ሥር ዋሉ

0
212

ማክሰኞ ጥቅምት 27 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በተለያዩ ድንበሮች በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመሻገር የሞከሩ 49 ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን፤ በኬንያ ናይሮቢ በሚገኙ ኹለት የተለያዩ ከተሞች ውስጥ በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የአገሪቷ ፖሊስ አስታውቋል።

የኬኒያ ፖሊስ ወደ ሌሎች አገራት ለመሻገር ሲሞክሩ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በቁጥጥር ሥር የሚውሉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ መምጣቱ እንዳሳሰበው ገልጿል።

አንዳንድ ፖሊስ ጣቢያዎች በበርካታ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች መጨናነቃቸውን ለዘ ስታር የገለጹት አንድ የአገሪቱ የፖሊስ መኮንን፤ ስደተኞቹን መመገብም ሆነ ከእነርሱ ጋር ከመግባባት አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ጥቅምት 22/2016 በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ኢትዮጵያዊያን አብዛኞቹ ትክክለኛ የኢሚግሬሽን የጉዞ ሰነድ አለመያዛቸውን ያስረዱት መኮንኑ፤ አንዳንዶች በእንግሊዝኛ ወይንም በኪስዋሂሊ መግባባት አለመቻላቸው ችግር መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡

አብዛኞቹ ስደተኞች በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች መጭበርበራቸውን የገለጹ ሲሆን፤ ወደሚሄዱበት አገር ለመንቀሳቀስ በመጠባበቅ ላይ እያሉ በአስከፊ ኹኔታ መጎዳታቸውን መኮንኑ ጨምረው ገልጸዋል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ አስቸኳይ እርምጃዎች እንዲወሰዱም ጠይቀዋል።

በዚህም ባለፈው ሐሙስ ማምሻውን 31 ስደተኞች ኮማሮክ በሚባል አካባቢ በሚገኝ ቤት ውስጥ አዘዋዋሪያቸውን በመጠበቅ ላይ እያሉ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ስደተኞቹ ከ14 እና 45 ባለው የእድሜ ክልል ውስጥ እንደሚገኙ ፖሊስ አስታውቋል፡፡

እነዚህ 31 ስደተኞች ወደ ካዮሌ ፖሊስ ጣቢያ ተወስደው ክስ የተመሰረተባቸው ሲሆን፤ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ እንደተወሰነባቸው ዘ ስታር በዘገባው አመላክቷል፡፡

በተጨማሪም ሌሎች 18 ኢትዮጵያውያን በጆን ሳጋ ሁሩማ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በሚገኝ መኖሪያ ቤት ውስጥ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ወደ ደቡብ አፍሪካ በማቅናት ላይ እንደነበሩ ለፖሊስ በአስተርጓሚ መናገራቸው ተገልጿል። ስደተኞቹ ከ15 እና 35 ባለው የእድሜ ክልል ውስጥ እንደሚገኙም ተመላክቷል፡፡

ስደተኞቹን በሕገ ወጥ መንገድ ሲያዘዋውሩ የነበሩ አዘዋዋሪዎች ለጊዜው በመሰወራቸው፤ በፖሊስ እየተፈለጉ እንደሚገኝም ተገልጿል።

የአገሪቷ ፖሊስ ከኢትዮጵያ የሚመጡ አብዛኛዎቹ ስደተኞች ወደ ደቡብ አፍሪካ እና መካከለኛው ምስራቅ ለማቅናት የሞያሌ መንገድን እንደሚጠቀሙ የገለጸ ሲሆን፤ ነገር ግን ወደ ቀጣዩ መዳረሻቸው ለመጓዝ በሚጠባበቁበት ወቅት በአገሪቱ በተለያዩ ቦታዎች ላይ በቁጥጥር ሥር እየዋሉ እንደሚገኙ አስታውቋል።

ከዚህ ቀደም መስከረም ወር ላይ አንድ ኢትዮጵያዊ በናይሮቢ 12 ኢትዮጵያውያንን በማዘዋወር ወንጀል ተከሶ፤ የ31 ዓመት እስራት እንደተፈረደበት አድስ ማለዳ መዘገቧ ይታወሳል።

ይበቃል ጌታቸው የተባለውና አዲናን ሞሐመድ ጋላኖ በሚል ተጨማሪ ሥም የሚታወቀው ይህ ግለሰብ የኬንያ መንግሥት ለውጭ አገር ዜጎች የሚሰጠውን ሐሰተኛ መታወቂያ ይዞ ሲንቀሳቀስ የነበረ ሲሆን፤ በኬንያ በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል 31 ዓመታትን በእስር እንዲያሳልፍ በናይሮቢ የሚገኝ ፍርድ ቤት ብይን አስተላልፎበታል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here