ከኢትዮጵያ ማግኘት ከሚገባኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ውስጥ ግማሹ ብቻ እያገኘሁ ነው ስትል ኬንያ ገለጸች

0
244

ማክሰኞ ጥቅምት 27 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት የኃይል ማመንጫ ግድቦች የውሃ መጠን ክፉኛ በመቀነሱ፤ ከኢትዮጵያ ማግኘት ከሚገባኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ውስጥ ግማሹ ብቻ እያገኘሁ ነው ስትል ኬንያ ገልጻለች፡፡

የኬንያ የኃይል እና የነዳጅ የካቢኔ ሚኒስትር ዴቪስ ቺርቺር፤ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ አሳሳቢ ድርቅ በመከሰቱ የኤሌክትሪክ ክፍያ መጠን ላይ ትልቅ ተጽእኖ አሳድሯል ሲሉ መግለጻቸውን ቢዝነስ ዴይሊ አፍሪካ የተሰኘው የንግድ ድረ-ገፅ ዘግቧል፡፡

ባለፈው የፈረንጆች ዓመት በኹለቱ አገራት መካከል በተገባ ውል መሠረት ኢትዮጵያ ለኬንያ 200 ሜጋዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለመሸጥ የተስማማች ቢሆንም፤ ድርቁ በኤሌክትሪክ ኃይል ዋጋ ላይ ባሳደረው ተጽዕኖ ምክንያት ለናይሮቢ የደረሰው የኃይል መጠን 100 ሜጋዋት ብቻ መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ሚስትሩ አክለውም፤ የኬኒያ ማሲንጋ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ ላለፉት ኹለት ወራት በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ውሃ ባለማግኘቱ ምንም አይነት ኤሌክትሪክ ማመንጨት አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡

ኬንያ ባለፈው ዓመት በጥር ወር ላይ ከኢትዮጵያ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ሃይል በርካሽ መግዛት የጀመረች ሲሆን፤ ይህን የሃይል አቅርቦት በሦስት ዓመታት ውስጥ እስከ 400 ሜጋ ዋት ድረስ ከፍ ለማድረግ እቅድ ተይዞ ነበር፡፡

አገሪቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአጎራባቾቿ አገራት የገዛችው የኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት በሦስት እጥፍ ማደጉን ከሳምንታት በፊት ማስታወቋም ይታወሳል።
ከዚህ ከአጎራባች አገራት ገዛሁት ካለችው የኤሌክትሪክ ሀይል ውስጥ 70 በመቶ የሚሆነውን የገዛችው ከኢትዮጵያ መሆኑን ቢዝነስ ዴይሊ ከኬንያ መንግሥት ያገኘውሁት መረጃ አመላክቷል ሲል ገልጿል፡፡

በተያያዘ የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ባለፈው ሐምሌ ወር በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለጎረቤት አገራት ከተደረገ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ከ102 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘት መቻሉን ማስታወቁን አዲስ ማለዳ መዘገቧ ይታወሳል፡፡

ገቢው ለጅቡቲ፣ ለሱዳንና ኬንያ ከሚቀርብ የኤሌክትሪክ የኃይል በሽያጭ መገኘቱን የገለጸው ተቋሙ፤ ገቢው ታቅዶ ከነበረው 143 ሚሊዮን ዶላር በአርባ ሚሊዮን ብር ገደማ ዝቅ ያለ እንደነበር አስታውቆ ነበር፡፡

የተገኘው ገቢ በ2014 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር ከጅቡቲ የተገኘው አራት በመቶ ጭማሪ ቢያሳይም፤ ከሱዳን የተገኘው ገቢ ግን 34 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን በመግለጽ፤ አገሪቱ በአሁኑ ጊዜ ከ50 ሚሊዮን በላይ ዶላር የተጠቀመችበትን የኤሌክትሪክ ሃይል ክፍያ አልፈጸሟን ገልጿል፡፡

ለኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ የተጀመረው በ2015 በጀት ዓመት መሆኑን የገለጸው ተቋሙ፤ በዚህም ከ46 ሚሊዮን በላይ ዶላር ለማግኘት ታቅዶ የተገኘው ገቢ 24 ሚሊዮን ዶላር ብቻ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ለዚህ ምክንያቱ “በኬንያ በኩል የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ የተጀመረው በግማሽ ዓመቱ ዘግይቶ በመሆኑና በኬንያ በኩል የነበረው ዝግጁነት አነስተኛ በመሆኑ ነው” ሲልም ገልጾ ነበር።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here