ባለስልጣኑ በአራት ወራት ውስጥ 13 ፋብሪካዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ

ኹለት አምራቾች ምርታቸዉን ከገበያ እንዲሰበስቡ ተደርጓል

0
212

ማክሰኞ ጥቅምት 27 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን በተያዘው በጀት ዓመት በመጀመሪያው አራት ወራት ውስጥ፤ የምግብ አምራቾች ላይ የድህረ ፍቃድ ቁጥጥር በማድረግ በ13 ፋብሪካዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል።

የባለስልጣኑ ምግብ ኢንስፔክሽንና ሕግ ማስፈጸም መሪ ሥራ አስፈፃሚ ሙላት ተስፋዬ የ2016 በጀት ዓመት በአራት ወራት አፈጻጸምን አስመልክተው እንዳስታወቁት፤ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በያዝነው በጀት ዓመት የመጀመሪያ አራት ወራት በተለያዩ 104 የምግብ አምራቾች ላይ የድህረ ፍቃድ ቁጥጥር አድርጓል፡፡

በዚህም መሰረት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በ2 የታሸገ ዉሃ አምራች፣ በ4 የዱቄት ፋብሪካና ብስኩት አምራቾች፣ በ2 የፍላቨር ጁስ መጠጥ፣ በ2 የአዮዳይዝድ ጨዉ፣ በ1 የምግብ ዘይት አምራች፣በ1 ቴስቲ ሶያ አምራች እና በ1 የወተት አምራች በድምሩ በ13 የምግብ አምራቶች ላይ ቁጥጥር ማደረጉን ገልጸው፤ በቁጥጥር ወቅት በታዩ የተለያዩ ክፍተቶች መሰረት ተደርጎ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል፡፡

ለምርት ደህንነት አስጊ የሆነ ደካማ የመልካም አመራረት ችግር፣ የሦስተኛ ወገን የላብራቶሪ ውጤት ምርት መውደቅ፣ ቴክኒካል ባለሙያዎች ሳይኖሩ ምርት ሲያመርቱ መገኘት፣ የአዮዲን መጠንና አለማሟላት፣ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈበት ጥሬ እቃ መጠቀም ፣የብቃት ማረጋገጫ አለማሳደስ እና የተሳሳተ ገላጭ ጽሁፍ መኖር ከታዩት ክፍተቶች መካከል ተጠቃሽ ምክንያቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በአጠቃላይ በቁጥጥር ወቅት በተጠቀሱት ችግሮች ምክንያት ክፍተታቸዉን አስተካክለዉ እስኪረጋገጥ ድረስ 13ቱ ፋብሪካዎች ምርት አምርተዉ ለኅብረተሰቡ እንዳያቀርቡ እገዳ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የተጣለ ሲሆን፤ በተጨማሪም ኹለት አምራቾች ምርታቸዉን ከገበያ እንዲሰበስቡ መደረጉን ሙላት አብራርተዋል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here