ረቡዕ ጥቅምት 28 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) ኢትዮጵያ ወደ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የምታደርገውን ጉዞ ለማሳካት መንግሥት አዋጆችን ከማጽደቅ አንስቶ ከተለያዩ የግል ተቋማት ጋር የዳታ ሴንተርን ለማስፋፋት እየሰራ እንደሚገኝ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የዳታ ማዕከላትን በማጠናከር ለኢትዮጵያ ለፋይናንስ ሴክተርና ለቴክኖሎጂ እድገት ለማዋል ያለመ የውይይት መድረክ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በዛሬው ዕለት ተካሂዷል፡፡
ውይይቱን የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ከአይቲ ፓርክ ኮርፖሬሽን እና ከዊንጉ አፍሪካ ጋር በመቀናጀት ያዘጋጁት ሲሆን፤ በመድረኩም ለግሉ የፋይናንስ ዘርፎች አስተማማኝ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ፈጣን የዳታ ሴንተር አገልግሎት ለመስጠት ምን መሰራት አለበት በሚል ጉዳይ ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡
በመድረኩ ኢትዮጵያ የዳታ ማዕከላትን ለማልማት ከተለያዩ አካላት ጋር እየሰራች መሆኑን የገለጹት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ/ር)፤ አሁኑ ላይ የዲጂታል ኢኮኖሚ ሽግግሩን የሚያግዙ የተለያዩ የዳታ ማዕከላትን ወደ ሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡
ከእነዚህም ውስጥ በአራት አፍሪካ አገራት ውስጥ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው ዊንጉ አፍሪካ በአይሲቲ ፓርክ ውስጥ ኢንቨስት ማድረጉን ለአብነት አንስተዋል፡፡
ሚንስትሩ አክለውም፤ ኢትዮጵያ ለምትገነባው ዲጂታል ኢኮኖሚ በፍይናንስ ዘርፉ የተሰማሩ ተቋማት ወጪ ቆጣቢ የዳታ ሥርዓት ሴንተርን መጠቀም እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡
የአይሲቲ ፓርክ ዋና ዳይሬክተር ሄኖክ አህመድ በበኩላቸው፤ የዳታ ሴንተር መስፋፋት የግል ተቋማት ከዚህ ቀደም የሚያስወጣቸውን ወጪ እንደሚቀንስ እና ሥራቸውን ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ መስራት እንዲችሉ እንደሚረዳቸው አስረድተዋል፡፡
አክለውም እንደ አገር በዳታ ሴንተር ሥርዓት ኢንቨስት የሚያደርጉ ድርጅቶችን ለመሳብና በዘርፉ ያለውን እምቅ አቅም ለመጠቀም በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ ከዊንጉ አፍሪካ በተጨማሪም በቀጣይ ወደ ገበያው የሚገቡ አስር የዳታ ማዕከላት በሂደት ላይ መሆናቸውን አመላክተዋል።
የየዊንጉ አፍሪካ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ተሾመ ወርቁ፤ የዲጂታል ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለማገዝና አገሪቱ በቀጣናው ያላትን የዲጂታል ቅንጅት ለማጠናከር ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የዊንጉ አፍሪካ በኢትዮጵያ ሥራ ከጀመረ 18 ወራት ማስቆጠሩን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ ድርጅታቸው በተለይም ደኅንነቱ የተጠበቀና አስተማማኝ የዳታ ሴንተር አገልግሎትን ለፋይናንስ ተቋማት በመስጠት ሥራቸውን ለማቅለል ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታውቀዋል፡፡



