በደቡብ ወሎ ዞን ያለው የጸጥታ ችግር በማዕድን ሐብት ልማት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደሩ

0
143

ሐሙስ ጥቅምት 29 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በ2016 በ1ኛ ሩብ ዓመት በማዕድን ሐብት ልማት ለበርካታ ባለሐብቶች ፈቃድ ቢሰጥም፤ የጸጥታ ችግሩ ወደ ሥራ ለማስገባት ተጽዕኖ ማሳደሩን የደቡብ ወሎ ዞን ማዕድን ሐብት ልማት መምሪያ አስታውቋል፡፡

ሆኖም ግን 6 ሺሕ 532 ኪሎ ግራም ኦፓል ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከ6 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን መምሪያው አመላክቷል፡፡

ደቡብ ወሎ የኦፓል፣ የድንጋይ ከሰል፣ የኦይል ሸል፣ የነዳጅ፣ የአምበር፣ የጃስፐር፣ የአጌት፣ የኦኒክስ፣ የቶርማሊን፣ የኳርቲዝ፣ የጅፕሰምና የሌሎች ከ30 በላይ የሚሆኑ ማዕድናት ባለቤት ስለመሆኑ ተረጋግጧል” ያሉት የዞኑ ማዕድን ሐብት ልማት መምሪያ ኃላፊ አህመድ አበባው፤ እነዚህንም የኢነርጂ፣ የጌጣጌጥና የኢንዱስትሪ ማዕድናት በሩብ ዓመቱ የመለየት ሥራ መከናወኑን አብራርተዋል፡፡

በዚህም ለ84 ባለሐብቶች አነስተኛ የማዕድን ሥራ ፈቃድ መሰጠቱን የተናገሩት የመምሪያው ኃላፊው፤ ከነዚህ ውስጥ 47 የሚሆኑት በሥራ ሂደት ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ 19 በሚሆኑት ላይ ደግሞ በተለያዩ ጥፋቶች ምክንያት ፈቃዳቸው እንዲሰረዝ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ አክለውም 42 ባህላዊ የማዕድን ሥራ ፈቃድ መሰጠቱ በመግለጽ፤ በዚህም ለ428 ነዋሪዎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል ብለዋል፡፡

12 ከፍተኛ ክሬቸር የምርት ፈቃድ መሰጠቱንም በመግለጽ፤ አራቱ በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኙና ቀሪዎቹ ደግሞ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ወደ ሥራ አለመግባታቸውን መግለጻቸውን አዲስ ማለዳ ከዞኑ ኮሙኒኬሽን መምሪያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል፡፡

የመምሪያው ኃላፊ በዚህ ሂደት በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት በዘርፉ የሚፈለገውን ያህል መሥራት አለመቻሉን የገለጹ ሲሆን፤ መሬትን ከሦስተኛ ወገን ነፃ አለማድረግ፣ የብድር አቅርቦት አለመመቻቸት፣ የኤሌትሪክ ኃይል አቅርቦት አለመኖር ሌሎች ያጋጠሙ ችግሮች መሆናቸውም አብራርተዋል፡፡

በተያያዘ ዜና በተያዘው የ2016 በጀት ዓመት የኦፓል ምርትን ለውጭ ገበያ በመላክ ሰባት ሚሊዮን 200 ሺሕ የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ፤ በሩብ ዓመቱ 324 ሺሕ 428 ዶላር ገቢ መገኘቱን የአማራ ክልል ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ አስታውቋል፡፡

በሩብ ዓመቱ 10 ሺሕ 959 ኪሎ ግራም የኦፓል ምርት ለውጭ ገበያ በመላክ ገቢው መገኘቱን የገለጸው ቢሮው፤ ይህም የኦፓል ምርት እሴት የተጨመረበትንና ያልተጨመረበትን የሚያካትት መሆኑን አመላክቷል፡፡

በተጨማሪም በተያዘው በጀት 18 ሺሕ 156 ኪሎ ግራም የኦፓል ምርት ለውጭ ገበያ በመላክ፤ ሰባት ሚሊዮን 200 ሺሕ የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጿል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here