በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) የወቅቱ ሊቀ መንበር አገሯ ጅቡቲ በመጪው ሐሙስ በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ውዝግብ እንዲሁም በሱዳን ጦርነት ዙሪያ ለመምከር አስቸኳይ ስብሰባ ጠርታለች።
የጅቡቲ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፤ የጅቡቲ ፕሬዝዳንት እስማዔል ዑማር ጊሌ አስቸኳይ ጉባዔው እንዲደረግ በመወሰናቸው በመጪው ሐሙስ ጥር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. በዩጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ አስተናጋጅነት እንደሚካሄድ አስታውቋል።
የኢጋድ አባል አገራት፣ የአፍሪካ ህብረት እንዲሁም የዓለም አቀፍ አጋር አካላት እንደሚሳተፉበት በተገለፀው በዚህ አስቸኳይ ጉባዔ የተጠራው በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል የነገሰውን ውጥረት እና ከስምንት ወራት በላይ የዘለቀውና አሁንም የቀጠለውን የሱዳን ጦርነት አስመልክቶ ነው።
ከሶማሊያ ራሷ ገንጥላ ከ30 ዓመታት በላይ ራስ ገዝ ግዛት የሆነችው ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር በታህሳስ ወር መጨረሻ የተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ፤ ለኢትዮጵያ የባህር ወደብ እና የባህር ኃይል መስፈሪያ የሚያስገኛት ሲሆን ሶማሊላንድ ደግሞ በሂደት መጠኑ የሚወሰን የኢትዮጵያ አየር መንገድ የገበያ ድርሻ እና የሉዓላዊ አገርነት እውቅና ይሰጣታል።
በአውሮፓውያኑ አዲስ ዓመት የተፈረመው ይህ የመግባቢያ ሰነድ ሶማሊያን ማስቆጣቱን ተከትሎ በአዲስ አበባ የተቀመጡ አምባሳደሯን መጥራቷ ይታወሳል።
የሶማሊላንድ እና ኢትዮጵያ መፈራረምን ተከትሎ ከተከሰቱ ዐበይት ጉዳዮች መካከል በሶማሊያ እና ሶማሊላንድ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ አካላዊ ጥቃት እና የንብረት ዝርፊያዎች እንደተፈፀሙ መሰማቱ እና በርካታ የድጋፍ እንዲሁም የተቃውሞ ሰልፎች ይገኙበታል።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ከቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስት ከሶማሊላንድ ጋር የመግባቢያ ሰነድ በመፈረሙ ሰበብ በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል የተቀሰቀሰው ዉጥረት እንዳሳሰበው ገልጾ ነበር።
በትላንትናው ዕለት ደግሞ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በኢትዮጵያና በሶማሌ ላንድ መካከል የተፈረመውን መግባቢያ ሰነድ “ያለልዩነት” እንቀበለዋለን ማለቱን አዲስ ማለዳ መዘገቧ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ መንግስት በዚህ ስምምነት የሚጎዳ አካልና ሀገር አይኖርም፤ የተጣሰ ሕግና የተሰበረ እምነትም የለም በማለት መግለጹ ይታወቃል። በተመሳሳይም ሶማሊላንድ ይህንን ስምምነት ለመቃረን የሚሞክር ማንኛውም አካል ይሁን ግለሰብ ላይ እርምጃ ወስዳለሁ በማለት አስጠንቅቃለች።
ከወራት በፊት የልማት በይነ መንግስታት ድርጅቱን እንደአዲስ የተቀላቀለችውን ኤርትራን ጨምሮ ጅቡቲ፣ ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ፣ ኬንያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን እና ዩጋንዳን በአባልነት ያቀፈው ኢጋድ፤ በሚቀጥለው ሳምንት ከሚያካሄደው ተጠባቂ አስቸኳይ ጉባዔ አስቀድሞ ከሰሞኑን የግብፅ፣ የሶማሊያ እና የኤርትራ መንግስት ባለስልጣናት በተደጋጋሚ በአካልና በስልክ መገናኘታቸው አይዘነጋም።


