“በትውልድ ላይ ሞት የሚያውጅ” የተባለው ስምምነት ከዚህ ወር ጀምሮ እንደሚተገበር ይጠበቃል

0
1708

ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአፍሪካ፣ ካሪቢያንና ፓስፊክ ሀገራት ድርጅት አባላት ጋር ለሚቀጥሉት 20 አመታት የሚቆይ ‘የንግድ እና ኢኮኖሚ ትብብር ስምምነት’ ከአውሮፓ ህብረት ጋር ሳሞዋ በተባለች አገር “የሳሞአ ስምምነት” የተባለውን ሰነድ ባሳለፍነው ህዳር ወር 2016 ለመፈራረም ተገናኝተው ነበር።

ኢትዮጵያም ይህንኑ ስምምነት በወከሏት አምባሳደር አማካኝት የፈረመች ሲሆን ስምምነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተያዘው ጥር ወር እንደሚፀድቅ እና ወደ ትግበራ እንደሚገባ ይጠበቃል ተብሏል።

ነገር ግን ‘ስለ ኢትዮጵያ ዝም አንልም ትውልድን ከግብረሰዶም እንታደግ’ ማህበር “በማር የተለወሰ እሬት የሆነ በትውልድ ላይ ሞት የሚያውጅ ስምምነት” ነው ብሏል። የኢኮኖሚ ትብብሩ እንዳለ ሆኖ ይህ ሰነድ በውስጡ ከያዛቸው የድጋፍ ስምምነቶች ጀርባ ለድጋፉ ምላሽ ፈራሚ አገራቱ “አካታችነት” በሚል የተጠቀሱ ነጥቦችን እንዲያሟሉ ይገልፃል።

ከእነሱም ውስጥ ግብረሰዶማዊነት፣ የፆታ መቀየር እና ውርጃን ሁሉን አቀፍ የወሲብ ትምህርት የመሳሰሉ አጀንዳዎችን በሰብአዊ መብት ሽፋንና በሌሎች አሳሳች ሀረጎች ተሰውረው የገቡበት በመሆኑ በበይነ መረብ የተቃውሞ ፊርማ ሲሰበሰብ አዲስ ማለዳ ተመልክታለች። 

“ይህ እንቅስቃሴአቸውን ከራሳቸው አልፎ በአለም ደረጃ ለማድረግ በየሀገራቱ መሰራጨት መጀመራቸውም የአደባባይ ሚስጥር ነው” የሚሉት በኢትዮጵያ የተቋቋመ የፀረ ግብረሰዶማዊነት ማህበር መስራች እና ሰብሳቢ መምህር ደረጀ ነጋሽ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት የኢትዮጵያ መንግስት በግረሰዶም ላይ ያለው አቋም ከለዘብተኛም ባለፈ እንዲስፋፋ የሚፈልግ ነው።

ደረጀ ነጋሽ “መንግስት በግረሰዶም ላይ ያለው አቋም ለዘብተኛ ብቻ ሳይሆን እንዲስፋፋም የሚፈልግ ነው፤ ለእርዳታ ብሎ መስማማቱ እና በየጊዜው እየጨመሩ መምጣታቸው የመከላከል ስራ እንደማይሰራ ማሳያ ነው በመሆኑም ምንም አይነት ቁርጠኝነት የለውም” ብለዋል።

በተጨማሪም “በህዝቡ ፊት መቃወምን እያሳዩ ከጀርባ ስምምነቶች መፈረም እና መሰል ድርጊቶችን ማድረግ አግባብነት የሌለው ነው” በማለት ገልፀዋል፡፡

ከዚህ ቀደም መሰል ድርጊቶች ጥቆማ እንዲሰርሱት የአዲስ አበባ ፖሊስ መግለጫ ማውጣቱን በማንሳት ከስምምነቱ ማለትም ከህዳር ወር በኋላ ያሉ ለውጦችን የማህበሩን ሰብሳቢ ጠይቀናቸዋል።

“አካታች (inclusive) ብለው እነሱ የሚሉት ማካተት ግብረሰዶምን፣ ፆታ መቀየር፣ ዝሙት የመሳሰሉትን የሚያካትት ማለታቸው ነው። በእኛ ግን አካታች ሲባል አካል ጉዳተኞችን፣ እርጉዝ እና ማየት የተሳናቸውን ጨምሮ የሚይዝ ማለት ነው ይህን ያላገናዘበ ውሳኔ መወሰኑን እንቃወማለን”በማለት አፅንኦት ሰተዋል፡፡

ስለ ኢትዮጵያ ዝም አንልም ትውልድን ከግብረሰዶም እንታደግ ማህበር “በማር የተለወሰ እሬት የሆነ በትውልድ ላይ ሞት የሚያውጅን ስምምነት በአግባቡ ሳያጤኑና ሳያረጋግጡ መፈረም አግባብ የለውም” ሲል አስታውቋል።

በጥቅምት እና ህዳር ወር 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ የግብረሰዶም ጉዳይ ሰፊ መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቶ ነበር። በርካታ ግለሰቦች በዚህ ድርጊት የሚታወቁ ሰዎችና ቦታዎችን በማህበራዊ ትስስር ገፆች እያጋለጡ፤ አልፎም አልፎም ይዘው ሲደበድቡ የሚያሳዩ ምስሎች መቅረባቸውን ተከትሎ ፖሊስ ጥቆማ አድርሱኝ ሲል መግለጫ አውጥቶ ነበር። የተለያዩ መዝናኛ ቦታዎችም በማህበረሰቡ ጥቆማ በፖሊስ ሲያዙ እና ቅጣት ሲደርስባቸው እነሱን ሲያስተናግዱ የነበሩ ቦታዎችም ሲታሸጉም ቆይቷል።

በማህበራዊ ሚዲያ የተቃውሞ ድምፅ ስብሰባም እየተካሄደ እንደሆነ እና ይህ የተቃውሞ ድምፅ መሳተፍ የሚፈልግ ሁሉ በቴሌግራም አማካኝነት መሳተፍ የሚችሉበት ነው የተባለ ሲሆን እስካሁን ከ100ሺ በላይ የተቃውሞ ድምፅ እንደተሰበሰበ እና ሂደቱም እየቀጠለ እንዳለ አዲስ ማለዳ ለማወቅ ችላለች፡፡

የዚህ የድምፅ አሰባሰብ ሂደት በማህበሩ እውቅና ያልተሰጠው ቢሆንም አካሄዱን እና እንቅስቃሴውን እንደሚደግፉ አቶ ደረጀ ገልጸዋል፡፡

ይህ አይነት ነገር በምንም መልኩ ኢትዮጵያ ውስጥ ተግባራዊ አይሆንም፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም “የሞት አዋጅ” ያፀድቃል ብሎ ማሰብ ይከበዳል፤ ከሆነ ግን የከፈለው ዋጋ ይከፈላል እንጂ ተግባራዊ እንዳይደረግ ቁርጠኝነታችን ይቀጥላል ሲሉ የማህበሩ ሰብሳቢ አሳስበዋል፡፡

የኢትዩጵያን ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ በቅርቡ ባወጣው መግለጫ “ጋብቻ አሁንም ወደፊትም በሴት እና በወንድ መካከል ብቻ የሚፈፀም ቅዱስ ሚስጢር ነው” ሲል  ማስታወቁ ይታወሳል። የኢትዩጵያን ካቶሊክ ቤተክርስቲያን በተመሳሳይ ጾታ ለሚደረግ ማንኛውም ነገር ፈቃድም ሆነ ቡራኬ እንደማትሰጥም አስታውቃለች።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here