“75 ሺህ የሚሆኑ አረጋውያን ላይ ሞት አንዣቧል”- የትግራይ ክልል አረጋውያን ማህበር

 

የትግራይ ክልል አረጋውያን ማህበር በስሩ የሚገኙ ጡረተኞችና አረጋውያን በጦርነቱ ማግስት ለከፋ ችግር መዳረጋቸውን የማህበሩ ሊቀ መንበር አርአያ ገሰሰ ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።

ከ75 ሺህ በላይ አርጋውያን እና ጡረተኛ አባላት ያሉት ማህበሩ፤ እንደሊቀ መንበሩ ገለጻ አሁን ላይ ከዚህ ቁጥር የሞቱና በህመም ላይ የሚገኙ ጥቂት አይደሉም።

በማህበሩ ውስጥ የሚገኙ ጡረተኞች ከሐምሌ 2013 እስከ ጥር 2015 ድረስ የጡረታ ደሞዝ ያልተከፈላቸው በመሆኑ እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውንም ሊቀ መንበሩ ገልጸዋል።

የሰሜኑ የኢትዮጵያ ጦርነት ከኹለት ዓመታት ደም አፋሳሽ ጉዞ በኃላ፤ በደቡብ አፍሪካ የተካሄደው ድርድር ጦርነቱ ሙሉ በሙሉ የቆመ ቢሆንም፤ በስምምነቱ ማግስት ከገዘፉ በርካታ ችግሮች መካከል ረሃብ ዋነኛው ነው። ስራ አጥነት፣ ህገ ወጥ ድርጊቶች እና ዝርፊያዎች እንዲሁም ስደት ተበራክቷል።

የፌደራል መንግስት “የለም ይሄ ለፖለቲካ ጥቅም ሲባል ነው የሚናፈሰው” ቢልም፤ የክልሉ ነዋሪዎች በረሀብ ክፉኛ መፈተናቸው ሲገልጹ የትግራይ ክልል ባለስልጣናት የተከሰተው ድርቅ ከ77ቱ ታሪካዊ ድርቅም የከፋ ነው በማለት በተደጋጋሚ ሲገለጹ ተሰምቷል።

በአጠቃላይ በክልሉ የሚገኘው ማህበረሰብ በድርቅና በበሽታ እየተጎዳ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ሆስፒታሎችም በሙሉ አቅማቸው ለህሙማን አገልግሎት መስጠት አለመቻላቸው ተገልጿል።

የትግራይ ክልል አረጋውያን ማህበር ሊቀ መንበር አርአያ ገሰሰ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት “በትግራይ የጥይት ድምጽ ቢቆምም አሁንም ሰዎች እየተራቡ እና እየሞቱ ነው”። ሊቀ መንበሩ አክለውም ይሄውም አረጋውያኑ “ምግብ፣ መድሃኒት ተቸግረዋል የቤት ኪራይ መክፈል አቅቷቸው ከዛሬ ነገ ያባርሩናል በሚል ስጋት ውስጥ ናቸው”ይላሉ።

“አረጋውያኑ በወጣትነት ዘመናቸው ለአገር ሲሰሩ የኖሩ ናቸው” ያሉት ሊቀመንበሩ፤ “አሁን ላይ በእርጅና እና በሕመም ምክንያት ወጥቶ መስራት አይችሉም፣ ስለዚህም ብቸኛ የሆነው መተዳደሪያቸው የጡረታ ደመወዝ ሊከፈላቸው ይገባል” ሲሉ ተደምጠዋል።

የአረጋዉያን ማህበሩ ሊቀ መንበር እንደገለጹት በክልሉ የሰብአዊ እርዳታ ላይ ተፈጸሟል በተባለው ስርቆት ምክንያት የሰብአዊ እርዳታ ተቋርጦ ነበር፤ “የስርቆት ወንጀል የፈጸሙ አካላትን ለፍርድ ማቅረብ ሲገባ፣ በረሃብ እየተቀጣ ያለው ግን ምንም የማያውቀው ማህበረሰብ ሆኗል”።

የአዲስ አበባ ብሔራዊ ማህበር የቅርጫፍ ቦርድ አባል የሆኑት እና የቀድሞ ፖሊስ ሰራዊት አባል ሀምሳ አለቃ ሞላ በበኩላቸው “በትግራይ በተለያዩ ወረዳዎች እና ዞኖች የሚገኙትን የማህበሩ አባላትን መቆጣጠር አልተቻለም” ብለዋል። ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ የገንዘብ እጥረት መኖሩንም ጠቅሰዋል።

በተመሳሳይ የሀምሳ አለቃ ሞላን ሀሳብ የሚጋሩት ሌላው አረጋዊ ሻምበል ጋሻ ገብረ ህይወት በጦርነቱ የሞተ ልጃቸውን ልጆች እየተንከባብ እንደሚገኙ እና የጡረታ ደሞዛቸው ባለመከፈሉ እጅግ እንደተቸገሩ ይገልጻሉ።

ሻምበል ባሻ አክለውም “በ19 ወር ደሞዝ ለቤት ኪራይ፣ ለምግብ እና ብድሮቼን ለመክፈል ነበር ዕቅዴ ግን አልሆነም። ገንዘባችን የት ሄደ? አሁን የቤት ኪራይ ስላከፈልኩ ፍርድ ቤት ለፍርድ ቤት እየተንከራተትኩ ነው” ይላሉ።

የኑሮ ውድነት ሌላው ፈተና መሆኑ የሚገልጹት ሻምበል ጋሻ አንድ ኩንታል ጤፍ 16 ሺህ ብር መሆኑን እንደ ምሳሌ ያነሳሉ።

“እኛ ወንጀል አልሰራንም። በዕድሜያችን የአረጋዊ ጡረታ ሲከለከል አይተንም አናውቅም” የሚሉት እኚው አረጋዊ “አንደኛውን አንሰጣችሁም ብለው ቢያሳርፉን ይሻላል። በየመስሪያ ቤቱ ደብዳቤ አስገባን አንዳች ምላሽ የሰጠን የለም” ሲሉ ምሬታቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የሞተው እና በህይወት ያለውን አሁን ላይ ማወቅ አለመቻሉን የገልጸው ማህበሩ፤ ለዚህም በትግራይ ያሉ በኤርትራ ወታደሮች እና በአማራ ክልል ታጣቂዎች የተያዙ ቦታዎች ላይ መንቀሳቀስ እንደማይቻልም አመላክተዋል።

የማህበሩ አባላት የአንድ ዓመት ከሰባት ወር የጡረታ ደሞዛቸውን እንዲከፈል ከአገር ውስጥ ጠበቃዎች ባሻገር በተለያዩ የዓለም ክፍል የሚገኙ ጠበቆችን ማናገራቸውን የገለጹ ሲሆን፤ በውጭ አገራት የሚገኙ ጠበቃዎች ፊርማ አሰባስባቹ ላኩ መባላቸውንም ለአዲስ ማለዳ ገለጸዋል።

ሆኖም አሁን ባለው ሁኔታ ፊርማ ለማሰባሰብ እንደማይችሉና በሁኔታውም ተስፋ መቁረጣቸውን ተስፋ በቆረጠ ድምጽ ይናገራሉ።

በአንዳንድ ዞኖች በሰላማዊ ሰልፍ ለ19 ወራት ያልተከፈላቸውን የጡረታ ደሞዝ መጠየቃቸውን እና የማህበሩ አመራሮችም ለክልሉ መንግስት እና ሌሎች ለሚመለከታቸው አካላት በተደጋጋሚ ጥያቄ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።

የትግራይ ክልል መንግስት ሰራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ተወካይ ተወልደ ለማ የጡረታ ደመወዝ የ19 ወራት አለመከፈሉን አረጋግጠው፤ ክፍያውን ማድረግ ያልተቻለው በክልሉ ለበርካታ ጊዜያት ደሞዝ መክፈል ተቋርጦ በመቆየቱ የጡረታ መዋጮ መሰብሰብ ባለመቻሉ መሆኑን ገልጸዋል።

ይሄን ክፍያ ለመፈጸም “ከእኛ አቅም በላይ ነው” የሚሉት ተወካዩ ተቋሙ ምንም አይነት ሌላ የገቢ ምንጭ የሌለው በመሆኑ የክልሉ መንግስት ለመንግስት ሰራተኞች ደሞዝ የመክፈል ሂደት ከጀመረ የጡረታ ክፍያም የሚከፈልበት ሂደት እንደሚኖር አመላክተዋል።

ለዚህም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ንግግር እየተደረገ መሆኑን ገልጸው የመንግስት ዉሳኔ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች መኖራቸውን አመላክተዋል። ጉዳዩን በተመለከተ ከፌዴራል የመንግሥት ማኅበራዊ ዋስትና አስተዳደር ምላሽ ለማግኘት አዲስ ማለዳ ያደረገችው ሙከራ ስብሰባ ላይ በመሆናቸው ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

በመላው ትግራይ 52 ወረዳዎች አባላት እና አመራሮች ያለው የትግራይ ክልል አረጋውያን ማህበር በአጠቃላይ በክልሉ በጦርነት ጊዜ የተፍናቀሉ፣ ከጦርነት በኃላ በድርቅ የተጎዱ የማህበረሰብ ክፍሎች መኖራቸው ለክርክር የሚቀርብ ባለመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት አስቸኳይ መፍትሄ በመስጠት ብዙሃኑን ከሞት መታደግ እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው አካላት አጽንዖት ሰጥተዋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here