‘ሞል ኢን አዲስ’ የተሰኘ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የገበያ ማዕከላት (ሞል) የስራ ቅጥርን ጨምሮ ንብረቱን ማስተዳደርና በቀላሉ ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል መተግበሪያ ይፋ ተደረገ።
ከከተማ ፕላን ጋር ተያያዥ የሆኑ ችግሮችን ይፈታል የተባለው እና በዛሬው እለት በኢሊሌ ሆቴል ይፋ በተደረገው ድረ ገጽ በቅርቡ የአንድሮይድ እና አይ ኦ ኤስ መተግበሪያዎች እንደሚኖሩት የአበልጻጊ ድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ መልካሙ ምትኩ ተናግረዋል።
ሞል ኢን አዲስ መተግበሪያ ለማህበረሰቡ ካሉበት ቦታ ሆነዉ በቀላሉ የሚፈልጉትን ምርት ወይም አገልግሎት እንደ ሲኒማ ቤት፣ ጸጉር ቤት፣ ባንክ ቤት፣ የሚከራዩ ቢሮዎችን፣ የስራ ማስታወቂያዎችን እናም ሌሎች መረጃዎችን የት አካባቢ እና የትኛዉ ሞል ላይ እንደሚያገኝ በካርታ ጭምር እንዲያገኙ ያስችላሉ ተብሏል። በተጨማሪም የስራ ማስታወቂያዎች ላይ አመልካቾች ካሉበት በመተግበሪያው እንዲያመለክቱ ያስችላል።
በቀጣዮቹ አራት ዓመታት ለ120 ሺህ ሰዎች የስራ ዕድል ለመፍጠር እንደታቀደ የሚገልጹት መልካሙ ምትኩ፤ በቀጣይ ድረ ገጹ የክፍያ አማራጮች ጋር እንዲተሳሰር ይደረጋል ብለዋል። በተጨማሪም ልዩ መስፈርቶች እንደሌሉ እና ማንኛውም የገበያ ማዕከል ተመዝግቦ ብቻ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችል ተገልጿል።
አዲስ ማለዳ ለዋና ስራ አስኪያጁ በአስተማማኝ ሁኔታ በየጊዜው መረጃዎች እየታከሉበት ስለሚሄድበት ሁኔታ ላቀረበችው ጥያቄ፤ “መልፋን ቴክ ለእያንዳንዱ የገበያ ማዕከል የራሳቸው ድረ ገጽ የሚያበለፅግ እና የሚቆጣጠር በመሆኑ መረጃዎች በየጊዜው እየተስተካከሉ ይቀርባሉ። በተጨማሪም ለገበያ ማዕከሉ ባለቤቶች በቀላሉ የማስተዳደሪያ መንገድ በመሆኑ ሁሉም የገበያ ማዕከላት የዚህ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ይጠበቃል” ሲሉ መልካሙ ምትኩ ገልጸዋል።
የመረጃ እና መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ዋና አማካሪ ደረጀ መኮንን እንደገለጹት ‘ሞል ኢን አዲስ’ በእስካሁን ሂደቱ ተደጋጋሚ የደህንነት ፍተሻ በኤጀንሲው በኩል ተደርጎለት በጥራት እያለፈ መጥቷል። የመልፋን ቴክ ዋና ስራ አስኪያጅ መልካሙ ምትኩ ከፍተኛው የደህንነት ቁጥጥር እንደሚደረግበት እና የግለሰቦች መረጃም የተጠበቀ እንደሚሆንና የኢትዮ ቴሌኮም የሆነ ሰርቨር እንደሚጠቀሙ አጽንኦት ሰጥተዋል። የኢንሳ ዋና አማካሪው ደህንነት፣ ተዓማኒነት እና ተደራሽነት ትኩረት እንደሚያስፍልጋቸው አስምረዋል።
‘ሞል ኢን አዲስ’ ሂደቶችን ለማመቻቸት፣ ምርታማነትን ለማሳደግ እና ወደር የለሽ የተጠቃሚ ተሞክሮን ለማቅረብ የተነደፈ ነው የተባለ ሲሆን ሌሎች ከተማዎችንም በመተግበሪያው ለማካተት እቅድ መያዙን አዲስ ማለዳ ማወቅ ችላለች።
መልፋን ቴክ ባለፉት ዓመስት ዓምታት ከ45 ለሚበልጡ ሰዎች የስራ እድል ፈጥሮ የብሔራዊ ኢንዱስትሪ ቋትን ጨምሮ ለተለያዩ ዘርፎች ዘመናዊ የአስተዳደር ስርዓት የሰራ እና በመስራት ላይ የሚገኝ የግል ድርጅት ነው።
በአዲስ አበባ ከተማ እስካሁን ከ640 በላይ የሚሆኑ የገበያ ማዕከላት የሚገኙ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ከ4 መቶ የሚበልጡት ምንም የኦንላይን ተደራሽነት የሌላቸው መሆናቸውን አዲስ ማለዳ የዋና ስራ አስኪያጁ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።


