ከዓለም አቀፍ ተቋማት ኢትዮጵያ በ2023 ሙሉ ዓመት በኢንተርኔት መዘጋት ከ1 ነጥብ 5 ቢልየን ዶላር በላይ አጥታለች በሚል የወጣውን ሪፖርት፤ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ ኩባንያው “ያህል ገንዘብ አላጣም” ሲሉ ገልጸዋል።
ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ በዛሬው ዕለት ጥር 14 2016 በስካይ ላይት ሆቴል የኢትዮ ቴሌኮምን የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ መንፈቅ ስራ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት መድረክ ይሄን መረጃ የሰራው አካል የመዘነበት መንገድ የጎንዮሽ ጉዳቶችን አማካይ ባደረገ መልኩ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመው፤ ሆኖም “ይሔ ቁጥር በቀጥታ ኢትዮ ቴሌኮምን የሚመለከት አይደለም” ሲሉ አክለዋል።
‘ቶፕ10ቪፒኤን’ የተሰኘው ድረ ገፅ ኢትዮጵያ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በኢንተርኔት መዘጋት ብቻ ከ1.59 ቢልየን ዶላር በላይ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ እንደደረሰባት ከሳምንታት በፊት የወጣውን ሪፖርት አዲስ ማለዳ መዘገቧ አይዘነጋም።

“ተቋማቱ መረጃውን ሲያጠናቅሩ በኢትዮጵያ ካለው ጠቅላላ ህዝብ አንጻር ሲለካ የኢትዮ ቴለኮም ገበያው ተደራሽ ባልሆነበት አካባቢ እንዲሁም የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ያልሆኑ አካላትን በማካተት ሲሰራ የመረጃ ልዩነት ሊፈጠር ይችላል” ሲሉም ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል።
የተፈጠረው አለመግባባት ነው የሚሉት ፍሬህይወት ታምሩ፤ ተቋሙ የራሱን ጥናት በማካሄድ የእርማት ሂደቶች እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
በ’ቶፕ10ቪፒኤንበ ድረ ገጽ ሪፖርት መሰረት ለ15 ሺህ ሰዓታት ገደማ በኢትዮጵያ ኢንተርኔት የተቋረጠ ሲሆን ይህም 29.8 ሚልየን ህዝብ ከኢንተርኔት ጋር ተለያይተው የቆዩበት ዓመት ሆኗል ብሏል።
በሌላ በኩል በኢትዮ ቴሌኮም የስድስት ወራት ሪፖርት በትግራይ ክልል አሁንም ጥገና ያልተደረገላቸው ቦታዎች መኖራቸውን ስራ አስፈጻሚዋ አንስተዋል።
ለዚህም እንደምክንያት የተጠቀሰው የጸጥታ ችግር እንዲሁም ሆነ ተብሎ በሚደረግ በቁሳቁሶች ስርቆት ሲሆን የጥገና ስራው ሙሉ ለሙሉ እንዳይጠናቀቅ ማድረጋቸው ታውቋል።
ሆኖም በትግራይ በተወሰኑ ከተማዎች 4G ኢንተርኔት አገልግሎት መጀመሩ ስኬት ሆኗል። በጦርነቱ ሳቢያ በክልሉ የተፈጠሩ ክፍተቶችን ለመሙላት መንቀሳቀስ በሚቻልባቸው አካባቢዎች የመሰረተ ልማት ሥራዎችን በመስራት የገንዘብ አቅምን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑ ተጠቁሟል።
የውጭ ምንዛሬ እጥረትም ከፈተናዎች አንዱ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን የውጭ ምንዛሬ ቴሌኮሙ በራሱ የሚያገኝበት መንገዶች ቢኖሩም፤ ዘርፉ ከፍተኛ የሆነ ኢንቨስትመንት የሚጠይቅ በመሆኑ ብቻውን በቂ አለመሆኑን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ገልጸዋል።

ስለሆነም በውጭ ምንዛሬ እጥረት የተለያዩ ሥራዎች እንዳይቋረጡ ከአጋር አካላት ጋር የውጭ ምንዛሬ የሚገኝበት ስራዎች እንዲሁም ከባንኮችም ጋርም የውጭ ምንዛሬ ፍላጎቱን ለማሟሟላት ጥረት እየተደረገ ይገኛል ተብሏል። የዋጋ ግሽበት በቴሌኮም ዘርፉ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩም ተመላክቷል።
በአጠቃላይ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ባጋጠሙ የጸጥታ ችግሮች ምክንያት አገልግሎት መቆራረጥ፣ በኔትዎርክ ሀብት ላይ የሚደርሱ አደጋዎች እንዲሁም የፋይበርና የኮፐር መስመሮች ስርቆትና መቆራረጥ፣ የቴሌኮም ማጭበርበር፣ የግንባታ ግብዓቶች እጥረት፣ የገበያ አለመረጋጋት፣ የኃይል አቅርቦት መቆራረጥ ዋነኛ ችግሮች እንደነበሩ ሪፖርቱ አመልክቷል።
ኢትዮ ቴሌኮም በግማሽ ዓመቱ 42 ነጥብ 86 ቢሊየን ብር አጠቃላይ ገቢ ያገኘ ሲሆን የደንበኞቹን ብዛት በአንድ ዓመት ውስጥ በ4 ነጥብ 7 ሚሊየን ማለትም 6 ነጥብ 7 በመቶ በማሳደግ 74 ነጥብ 6 ሚሊየን ማድረሱን አዲስ ማለዳ ከሪፖርቱ ተመልክታለች።
በመንፈቅ ዓመቱ ከተሰሩ የሞባይል ማስፋፊያዎች መካከል ለገጠር ቀበሌዎች የሚውል በ10 ክልሎች፣ ለ41 ወረዳዎች፣ 229 ሺህ ደንበኞችን ማስተናገድ የሚችሉ 41 አዲስ የሞባይል ጣቢያዎች ተተክለው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል።


