የ30 ዓመታት የባህር በር እና የሉዓላዊነት ፍላጎትን የያዘው ስምምነት የሦስት ሳምንታት ሂደት

0
964

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቤሂ ኢትዮጵያ የባሕር በር የምታገኝበትን የመግባቢያ ስምምነት ታህሳስ 22 ቀን 2016 ተፈራርመዋል። የስምምነቱን መፈረም ተከትሎ በርካቶች ድጋፋቸውንና ተቃውሟቸውን፤ ተስፋቸውን እና ስጋታቸውንም እየገለጹ ይገኛሉ። 

ከኢትዮጵያ ጋር በተለይም ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጀመር በኋላ ግንኙነታቸው የሻከረው ግብጽ በሶማሊያ ጉዳይ ድርድር አላውቅም ስትል መግለጫ በመስጠት ለሶማሊያ ድጋፋቸውን ካሳዩ አገራት አንዷ ሆናለች። 

በፕሬዝዳንት አብዱልፈታን አልሲሲ ግብዣ ወደካይሮ የተጓዙት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼህ ማህሙድ ከግብጽ አጋራቸው ጋር ባወጡት መግለጫ የግብጽ ፕሬዝዳንት የአረብ ሊግ አባል በሆነችው አገረ ሶማሊያ ላይ ምንም አደጋ አንታገስም ብለው፤ የኢትዮጵያ መንግስትንም በሶማሊያ የግዛት አንድነት ውስጥ ጣልቃ በመግባት ወንጅለዋል።

ከቀናት በፊት የሶማሊያ እና ግብጽ መሪዎች በጋራ በሰጡት መግለጫ የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ “ግብጽ ማንም በሶማሊያ ላይ ስጋት እንዲደቅንባት ወይም ብሄራዊ ደኅንነቷን እንዲጎዳ አትፈቅድም” በማለት ገልጸዋል።

አል ሲሲ አክለውም “ወንድሞቻችን በተለይ ጣልቃ እንድንገባ ከጠየቁን በዚህ ጉዳይ ባትፈትኑን ይሻላል” ያሉ ሲሆን  “ኢትዮጵያ ወደብ የማግኘት መብት ቢኖራትም በሌሎች አገራት ግዛት ውስጥ በህገ ወጥ መንገድ እጇን ማስገባቷን ግብጽ ትቃወማለች” በማለትም መልዕክት ለኢትዮጵያ አስተላልፈዋል።

የግብጹን ፕሬዝዳንት መልዕክት ተከተሎም የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ የብሄራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በኤክስ ገጻቸው “ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሰላም እና ደህንነት ለማስጠበቅ የውድ ልጆቿን ላብ እና ደም ገብራለች፤ ሁለቱ አገራት ድንበር ተጋርተው ብቻ የሚኖሩ ሳይሆን ቋንቋ እና ባህል የሚጋሩ ወንድማማች ህዝቦች ናቸው” በማለት አስፍረዋል።

አምባሳደር ሬድዋን አክለውም “ሶማሊያ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በነበረችበት ወቅት ብዙም ድጋፍ ያልሰጧት አካላት አሁን ራሳቸውን እንደ እውነተኛ ወዳጅ እያቀረቡ ያሉት፤ ለሶማሊያ ካላቸው ወዳጅነት ይልቅ ለኢትዮጵያ ባላቸው የጠላትነት ስሜት ነው” ሲሉም ገልጸዋል። እንዲሁም አጀንዳቸው ከሰላም ይልቅ እንዲፈጠር የሚፈልጉት አለመግባባት እና ትርምስ ነውም ብለዋል።

ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ቀጠናዊ ትብብር ለማጎልበት ከሁሉም ጎረቤት አገራት ጋር በትብብር መንፈስ መነጋገር የምትሻ መሆኑና “ቀጣይነት ያለው ንግግር” የተሻለ አማራጭ መሆኑን እንደምታምን የብሄራዊ ደህንነት አማካሪው አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ የባህር በር በኪራይ ማግኘት እራሷን ችላ እንዳትቆም ለሚፈልጉ አገራት፣ በተመሳሳይም ለኢትዮጵያ የወደብ ኪራይ የምትሰጠው ጅቡቲ እንዲሁም ታይዋን ወደ ግዛቴ ትመለሳለች የምትለው ቻይናን ጨምሮ የኢትዮጵያን ስምምነት በስጋት ዓይን የሚመለክቱ አካላት ተበራክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አርብ ጥቅምት 2 ቀን 2016፤ በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በተላለፈውና ‹‹ከጠብታ ውኃ እስከ ባሕር ውኃ›› በሚል ርዕስ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ባደረጉት ገለጻ፤ “አባይና ቀይ ባህር የኢትዮጵያን ልማትና ጥፋት የሚወስኑ የኢትዮጵያ የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ናቸው” ሲሉ ገልጸዋል።

“በዓለም ላይ 120 ሚሊዮን ሕዝብ ኖሮት የባህር በር የሌላት አገር ኢትዮጵያ ብቻ ናት” የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የኢትዮጵያ የሕዝብ ቁጥር እየበዛ በመሆኑ አሁን ባለው አሰራር መሸከም የማይቻል በመሆኑ እየቆየ ሲሄድ ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ጉዳት ያመጣል ሲሉም አሳስበዋል።

ከሰሞኑን በዩጋንዳ ካምፓላ በተካሄደው 19ኛው የገለልተኛ ሀገራት ንቅናቄ የመሪዎች ጉባኤ ላይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ንግግር “ወደብ የሌላቸው ሀገራት የህዝቦቻቸውን በቂና ቀጣይነት ያለው ደረጃውን የጠበቀ የመኖሪያ ሁኔታዎች ፍላጎትን ለማሟላት እና እድገታቸውን ለማረጋገጥ ፈተና እየገጠማቸው ነው” ማለታቸው አይዘነጋም። 

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻም የኢትዮጵያ የወደብና የባህር በር አማራጮች ውስጥ ዘይላ፣ የጀቡቲ ወደብ፣ አዶሊስ፣ ምፅዋና አሰብ ሲሆኑ “መተንፈሻ በር በየትኛውም ከመጣ በግዢም ይሁን፣ በሊዝም ይሁን በሆነ መንገድ በስምምነት ከመጣ የምንፈልገው እሱን ነው” ሲሉ አጽንዖት ሰጥተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ገለጻ ተከትሎ የኤርትራ መንግሥት የመረጃ ሚኒስትር ባወጣው አጭር መግለጫ፤ “በቅርብ ጊዜ ስለ ውሃ እና ስለ ባህር በሮች እንዲሁም ተመሳሳይ ርዕሰ ጉዳዮች የተነገረው እና የተባለው ቁጥር የለውም፤ በዚም ያልተገረመ ታዛቢ የለም” በማለት ለኢትዮጵያ አጸፋዊ ምላሽ  ሰጥቷል።

በተመሳሳይም የሶማሊያ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አሊ ኦማር “የሶማሊያ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት እንዲሁም መሬት፣ ባህር እና አየር በሕገ መንግሥታችን እንደተደነገገው ለድርድር ክፍት አይደለም” ሲሉ ተናግረው ነበር። 

ከተፈረመ 23 ቀናት ያስቆጠረው ይሄው ስምምነት ታድያ በኢትዮጵያ እና በሶማሊላንድ ነዋሪዎች ዜናው መሰማቱን ተከትሎ በርካቶች በአደባባይ በመውጣት ደስታቸውን ሲገልጹ ተስተውለዋል። በአንጻሩ ሶማሊያውያን ደግሞ ስምምነቱን በመቃወም “ዋን ሚሊየን ማርች” የተሰኘ ተቃውሞ መጀመራቸው አይዘነጋም። 

በስምምነቱ ማግስት የሱማሊያ መንግስት ካቢኔ ኢትዮጵያና ሱማሌላንድ በደረሱበት የቀይ ባሕር በር ስምምነት ዙሪያ አስቸኳይ ስብሰባ መቀመጡ እንዲሁም በኢትዮጵያ የሚገኙ አምባሳደሩን መጥራቱ ይታወቃል።

የሶማሊያ መንግሥት የአገሪቱ ካቢኔ ካደረገው አስቸኳይ ስብሰባ በኋላ ባወጣው መግለጫም፤ ኢትዮጵያ የሶማሊያ አካል ከሆነችው ሶማሊላንድ ጋር የደረሰችው ስምምነት ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም ብሎ ነበር። እንዲሁም ስምምነቱ ሕጋዊ መሠረተ የሌለው እና ተፈጻሚ ሊሆን የማይችል ነው ሲልም አጣጥሎታል።

እንዲሁም የሶማሊያ መንግስት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአፍሪካ ህብረት፣ የእስላማዊ ትብብር ድርጅት፣ የአረብ ሊግ፣ የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት (ኢጋድ) እና ሌሎች ቀጠናዊ እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ከጎኗ እንዲቆሙ እና ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ሕጎች እንድትገዛ ጫና እንዲያሳድሩ ጥሪ አቅርቦ ነበር።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የአውሮፓ ኅብረት፣ የአፍሪካ ህብረት፣ ኢጋድ፣ አረብ ሊግ እንዲሁም አገራት በተናጠል ባወጧቸው መግለጫዎች የሶማሊያን አቋም ደግፈው ኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በመጣስ እና የግዛት አንድነት ላይ አደጋ በመሆን ወንጅለዋል። 

የኢትዮጵያ መንግስት ኮምኒኬሽን አገልግሎት በበኩሉ “በዚህ ስምምነትም የሚጎዳ አካልም ሆነ ሀገር አይኖርም፣ የተጣሰ ሕግና የተሰበረ እምነትም የለም” ሲል የገለጸ ሲሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ በተደጋጋሚ ይህንኑ አቋም አጽንተው እየገለጹ ይገኛሉ።  

የኢትዮጵያ መንግስት ነገር ግን በዚህ አዎንታዊ ድምዳሜ የሚከፋ፣ የሚደነግጥና ሁኔታውን ለማደፍረስ የሚንቀሳቀስ አካል አይኖርም ማለት አለመሆኑንም ጠቁሟል። “ላለፏት 30 ዓመታት የባህር በር አልባ ሆና መቆየቷን፤ የታሪክ ስብራትና የትውልድ ቁጭት ለማረም” በሚል መንግስት የአገሪቷን ቁመናና ዕድገት የሚመጥን ዘላቂና አስተማማኝ የወደብና የባሕር በር አማራጮችን ስለማስፋት ሲያውጠነጥንና ሲመክርና ሲሞክር መቆየቱም ተገልጿል።

ከሶማሊላንድ ጋር በጋራ ተጠቃሚነት ጉዳዮች ለወራት ምክክር እና ድርድር ከተካሄደ በኋላ ሁለቱንም አካላት ተጠቃሚ በሚያደርግ አግባብ የመግባቢያ ሰነዱ መፈረሙን የአገራቱ መንግስታት አስታውቀዋል። 

ይኸው ሰነድ ለኢትዮጵያ በኤደን ባህረሰላጤ ላይ ዘላቂና አስተማማኝ የባሕር ኃይል ቤዝና ኮሜርሻል ማሪታይም አገልግሎት በሊዝ የምታገኝበትን ዕድል የሚስገኝ ሲሆን በአንጻሩ ሶማሌ ላንድን ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሊዙ የሚታሰብ ድርሻ እንዲኖራት እንደሚያስችል ተገልጿል።

እንዲሁም በርካቶችን ያሰጋው እና ቅሬታ የፈጠረው፤ ሶማሊላንድ ላለፉት 30 ዓመታት ተነፍጓት የቆየውን ዕውቅና ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት አሁን የወሰነው ጉዳይ እንደሌለና በጥልቀት አጢኖ አቋም የሚወስድበትን አግባብ መኖሩንም ተጠቁሟል።

የተደረገው ስምምነት መንግሥት የኢትዮጵያን መሻቶች ከጎረቤቶቿ ጋር በሚደረግ ትብብር፣ በሰጥቶ መቀበልና በሰላማዊ መንገድ ብቻ ለማሳካት ያለውን እምነት በተግባር ያሳየ እና ዕድሉ ለሁሉም ክፍት የነበረና ክፍት ሆኖም የሚኖር ነው ቢባልም ሶማሊያ እና አጋሮቿ አልወደዱትም።

በአንጻሩ ኢጋድ በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል የተፈጠረውን ሁኔታ በጥንቃቄ እየተከታተለው እንደሚገኝ ገልጾ፤ በቀጠናው ሰላም ላይ የሚኖረውን ተጽእኖ እንደሚገነዘብም ገልጾ ነበር።

ታህሳስ 28 ቀን 2016 የሶማሊያው ፕሬዝደንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የገባችውን ስምምነት “ውድቅ የሚያደርግ” ያሉትን ሕግ ፈርመው ካጸደቁ በኋላ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ይህ ሕግ “አንድነታችንን እና ሉዓልዊነታችንን እንዲሁም የግዛት አንድነታችንን ለመጠበቅ ወሳኝ ነው” ብለዋል።

የስምምነቱ ፈራሚ አገር የሶማሊላንድ መከላከያ ሚንስትር ከኢትዮጵያ ጋር የተደረሰውን ስምምነት በመቃወም ስልጣናቸውን መልቀቃቸውም የተሰማ አስገራሚ ዜና ነበር። ይሁን እንጂ ሶማሊላንድ ይህንን ስምምነት ለመቃረን የሚሞክር ማንኛውም አካል ይሁን ግለሰብ እርምጃ እንደሚወሰድበት አስጠንቅቃለች።

የኢትዮጵያ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እና የሶማሊላንድ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ሜጀር ጄነራል ኑህ ኢስማኤል ታኒ በወታደራዊ ትብብር ዙሪያ አብረው ለመሥርታ የሚያስችላቸውን ውይይት ማድረጋቸው የሶማሊያ ስጋትን ጨምሮታል።

ይኽን ተከትሎም ታህሳስ 29 ቀን 2016 የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወደ ኤርትራ፣ አሥመራ ተጉዘዋል። በተመሳሳይም ከቀናት በኃላ የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሹኩሪን ተቀብለው አነጋግረው ነበር።  

ጥር 2 ቀን 2016 ደግሞ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በኢትዮጵያና በሶማሌ ላንድ መካከል የተፈረመውን መግባቢያ ሰነድ በተመለከተ የስምምነቱን ማዕቀፍ፣ ዝርዝር ይዘቱን እና ከስምምነቱ ጋር ተያይዞ ባሉት እድሎችና ስጋቶች ላይ በዝርዝር ከተወያየ በኋላ ስምምነቱን ያለልዩነት የሚደግፉ መሆኑን ገልጿል።

ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ እና እናት ፓርቲ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አቋምን የተቃረነ መግለጫ በይፋ ያወጡ የፖለቲካ ድርጅቶች ናቸው። ጥር 9 ቀን 2016 ባልደራስ ፓርቲ ባወጣው መግለጫ “ኢትዮጵያን ለቀውስ” ባለው ስምምነት የብልጽግና መንግስት “በቅርቡ የደረሰበት የመግባቢያ ሰነድ ፊርማ “በራዕይነት ያነገበዉን የኦሮሚያ ሪፓብሊክን የባህር በር ለማስገኘት አልያም በእጅ አዙር የውጪ ኃይሎችን ፍላጎት ለማሟላት ካልሆነ በስተቀር፣ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ያማከለ ነዉ ለማለት አይቻልም” ሲል ተችቷል።

ፓርቲው አክሎም “ስምምነቱ ዳር ድንበሯ ዓለም አቀፍ እዉቅና ከሌላት፣ የሱማሊያ ሪፐብሊክ አንድ አካል ከሆነች ግዛት ጋር መሆኑ አገራችንን በኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች በመደገፍ ላይ ካለችዉ ከሶማልያ ጋር ወደማያባራ የጦርነት አዙሪት የሚከተን መሆኑ አጠራጣሪ አይደለም” ሲል አጽንዖት ሰጥቷል። ባልደራስ አያይዞም “የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የወሰደው ጭፍን የአድርባይነት የድጋፍ አቋም መግለጫ የፓርቲያችን የባልደራስ አቋም አይደለም” በማለት አስታውቋል።

ከባልደራስ በመቀጠል ስምምነቱን የተቃወመው እናት ፓርቲ ዓርብ ጥር 10 ቀን 2016 ባወጣው መገለጫ መንግስት ከሶማሌላንድ ጋር በተፈራረመው ሰነድ ምክንያት ከሶማሊያ ጋር የተጀመረው ፍጥጫ ቀስበቀስ ወደ ኃይል አማራጭ አድጎ “ጉዟችን ከድጡ ወደ ማጡ” እንዳያደርግ ትልቅ ስጋት አለኝ ሲል ገልጧል።

ድርጊቱን “ኢትዮጵያን ከመሰለች ጥንታዊት፣ ታሪካዊት  እና የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኝ አገር የማይጠበቅ ድርጊት ነው” ሲል የኮነነው እናት ፓርቲ፤ የሶማሊያ መንግሥት ጉዳዩን አግዝፎ ወደ ኃይል ፍጥጫ ከመሻገር ይልቅ ሰከን ባለ መልኩ ጉዳዩን ተመልክቶ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔዎችን ብቻ በመከተል ስጋቱን ለመቅረፍ እንዲሰራ ጠይቋል።የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ውዝግብ ዙሪያ አስቸኳይ ስብሰባ መጥራቱ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ግንኙነት መሻከር እና ውጥረት መባባስን ተከትሎ የተጠራው የአረብ ሊግ አስቸኳይ ጉባዔ የሶማሊያ ሉዓላዊነት ተጥሷል የሚል ጠንካራ የአቋም መግለጫ ባለፈው ሳምንት አውጥቷል።

የአረብ ሊግ መግለጫ በኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ መካከል የተፈረመውን የመግባቢያ ስምምነት ከሶማሊያ ጎን በመሰለፍ “ባዶ እና ተቀባይነት የሌለው ዓለም አቀፍ ህግን የጣሰ” ነው ቢልም  የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በኤክስ ገጻቸው ኢትዮጵያ የአረብ ሊግ አቋምን በፍጹም አትቀበልም በማለት አስፍረዋል።

የወቅቱ የአረብ ሊግ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊቀ መንበር አገር የሆነችው የመን ባሰናዳችውና በበይነ መረብ አማካኝነት የተደረገው የአረብ ሊግ አስቸኳይ ጉባዔ ለሶማሊያ አንድነት፣ ሉዓላዊነት እና የግዛት ጥበቃ ጽኑ ድጋፍ ለማድረግ የተስማሙበትን አቋም ይፋ አድርገዋል።

በአገራቱ አቋም መሰረት የሶማሊያን ሉዓላዊነት ጥሶ የተፈረመውን የመግባቢያ ስምምነት ከሶማሊያ ጎን ሆነው ውድቅ ማድረጋቸውን እንዲሁም የሶማሊያን ወቅታዊ የውስጥ ችግር እንደመልካም አጋጣሚ ተጠቀመው የሚደረጉ ጥሰቶችን እንደሚያወግዙ አስታውቀዋል። 

አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ እንደገለጹት ደግሞ “ኢትዮጵያ የአረብ ሊግን መግለጫ አጥብቃ ትቃወማለች። ኢትዮጵያ ከበርካታ የአረብ አገራት ጋር ጥሩ የሁለትዮሽ ግንኙነት የምታራምድ ቢሆንም የአረብ ሊግ ግን የጥቂቶችን ፍላጎት እያስፈፀመ ነው”ይላሉ።

የኢትዮጵያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ “በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ እና ሉዓላዊነት ላይ ጣልቃ ለመግባት የሚደረግ ሙከራ ነው” ያሉት ይኸው መግለጫ የሶማሊያ ሪፐብሊክ መንግስት “የተጋረጠበትን የሉዓላዊነትና ጣልቃ ገብነት አደጋ” ለመቀልበስ የኢትዮጵያ መንግስትን በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት እንዲጠይቅ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጿል።

የአሜሪካ መንግስት በተመሳሳይ ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ስምምነት በቀጣናው የሚንቀሳቀሰው እና “የአል ቃይዳ የሽብር ቡድን” አጋር ነው በሚባለው የአል ሸባብ ቡድን ላይ የሚወሰደውን እርምጃ እንደሚያደናቅፍ ስጋቱን አስታውቋል።

ቻይና በበኩሏ ከሶማሌላንድ ጋር የተደረሰውን ስምምነት በተመለከተ ለሶማሊያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ድጋፏን እንደምትሰጥ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የሆኑት ማኦ ኒንግ ገልጸዋል።

ቃል አቀባዩ አክለውም “ቻይና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻርተር አላማዎችን እና መርሆችን ለማስከበር የቆመች አገር ነች” ያሉ ሲሆን ሶማሊላንድ የሶማሊያ ግዛት ነች” ሲሉም ተናግረዋል።

ሶማሊያ በተቃውሞዋ የጸናች ሲሆን የአፍሪካ ኅብረት የሰላም እና የጸጥታ ምክር ቤት ካደረገው ስብሰባ በኋላ ሁለቱ አገራት “ትርጉም ያለው ንግግር” በማድረግ ችግራቸውን እንዲፈቱ መጠየቁን ተከትሎ፤ ሶማሊያ ጥር 9 ቀን 2016 ባወጣችው መግለጫ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችውን የመግባቢያ ስምምነት እስካላነሳች እና ለሶማሊያ የግዛት አንድነት ማረጋገጫ እስካልሰጠች ድረስ ከአዲስ አበባ ጋር ለሚደረግ ሽምግልና ቦታ እንደሌላት ገልጻለች።

ለበርካታ ዓመታት ለሶማሊያ የጎን ውጋት ሆኖ የቆየው አሁንም ዋነኛ ስጋቷ የሆነው የአል ሸባብ የታጣቂዎች ቡድን፤ በተደረሰው ስምምነት ለሶማሊያ መንግስት ድጋፉን አሳይቷል። 

በኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ መካከል በታህሳስ ወር መጨረሻ የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ በርካታ ድጋፍ እና ተቃውሞ እየገጠመው ሲሆን የተፈራረሙት አገራት አሁንም በስምምነቱ የተጣሰ ህግ እንደሌለ ደጋግመው በመግለጽ ሙግታቸውን ቀጥለዋል።

በርካቶችም ይሄ ጉዳይ የት ይደርሳል? ሲሉ የሚጠይቁ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ምኞታቸውን፣ ስጋታቸውን እና ቅሬታቸውን መግለጻቸውን ቀጥለዋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here