የጋዜጠኞች እስር ዓመታዊ ሪፖርት ማግስት በኢትዮጵያ አንድ ጋዜጠኛ ታስሯል

0
730

ኢትዮጵያ እስከ ህዳር ድረስ በነበሩት 12 ወራት ውስጥ ታስረው የተፈቱ ጋዜጠኞችን ሳይጨምር ስምንት ጋዜጠኞች በማሰር ከአፍሪካ አገራት ሶስተኛ ደረጃ መያዟን ሪፖርት አመላክቷል። 

ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች (ሲፒጄ) ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ባወጣው ዓመታዊ ሪፖርቱ እንዳስታወቀው በአፍሪካ በታሳሪ ጋዜጠኞች ብዛት ቀዳሚውን ቦታውን የያዘችው ኤርትራ ስትሆን፤ ግብጽ ሁለተኛ ቦታን ይዛለች።

በአፍሪካ እስካለፈው ህዳር መጨረሻ ድረስ ባለው የአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ፤ ቢያንስ 67 የሚሆኑ ጋዜጠኞች “ከስራቸው ጋር በተያይዘ ለእስር መዳረጋቸውን” ሲፒጄ በሪፖርቱ አመልክቷል።

ይህንን ተከትሎ ኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት የሚዲያ ነጻነት ጥያቄ ውስጥ የሚገባባት አገር መሆኗ ጥያቄ የተነሳ ሲሆን ዓመቱ የጋዜጠኞች መታሰር እንዲሁም ከመንግስት የመገናኛ ብዙኀን ተቋም ጭምር ከሀገር መውጣት ተስተውሏል። 

አገር በቀል መንግስታዊ ያልሆነው የመብቶች እና የዲሞክራሲ እድገት ማዕከል (ካርድ) በቅርቡ ይፋ ባደረገው የሚዲያ ቦታ እና የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ማህበራት ሁኔታ የጥናት ጽሁፍ የገዢው መንግስት ብልጽግና ፓርቲ ከመጣበት ጊዜ አሁን እስካለበት ድረስ የሚዲያዎች ነጻነት ያለበትን ሁኔታ የዳሰሰ ነበር።

በጋዜጠኞች አፈና እና የእነርሱን ማንነት ለመግለጽ ፈቃደኛ ባለመሆኑ በመብት ጥሰት የሚደረጉ ተግዳሮቶችን እንዲሁም ከፍርድ በፊት ረዘም ያለ ጊዜ በእስር ማቆየትን ጥናቱ አመላክቶ ነበር።

በዚህ ወቅት በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞች (በሲፒጄ መረጃ)

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የተከሰሱ ሰዎችን ከቅድመ ችሎት ማሰርን በግልፅ የሚከለክል ህግ በመገናኛ ብዙኃን ላይ የሚፈጸም ወንጀል በመሆኑ ስለ ህገ-ወጥ ድርጊቶች እንደሚያሳስበው ገልጾ ቅድመ-ፍርድ ቤት እስራት፣ የጉብኝት መብቶች መከልከል እንዲቆምና የሚዲያ ህጉ እንዲከበር ደጋግሞ ጠይቋል። 

በገለልተኛ ሚዲያ ላይ ከፍተኛ ጫና ስለመኖሩ እና በአንቀጽ 29 የተደነገገውን የሚዲያ ነጻነት እንዲሁም መረጃ የማግኘት መብት የሚጥስ ተግባር በመንግስት አካላት እየተፈጸመ እንዳለም አዲስ ማለዳ ከ’ካርድ’ ጥናት ተመልክታለች። 

ይህ በእንዲህ እንዳለ “ከዘ-ሐበሻ ሚዲያ ጋር ግንኙነት አለህ በሚል የጋዜጠኛ ሄኖክ ዓለማየሁ ወንድም የሆነው ጋዜጠኛ አብነት ታምራት 10 የሚሆኑ የመንግስት ደህንነቶች ዓይኑን በጨርቅ ሸፍነው አፍነው ወሰዱት” ሲል ዘ-ሐበሻ ዘግቧል።

ፖሊስም “በሽብርተኝነት ወንጀል መጠርጠሩን” እንደገለፀለትና ሰኞ ጠዋት ቤተሰቦቹ “ፍርድ ቤት ያቀርቡታል” በሚል ጠበቃ ይዘው የጊዜ ችሎት ሲጠብቁ አለመቅረቡንም አዲስ ማለዳ ከዘ-ሐበሻ ዘገባ ተመልክታለች። 

በአንጻሩ የገዢው መንግስት ወደ ስልጣን ሲመጣ በመቶዎች የሚቆጠሩ የዜና ድረ-ገጾችን እገዳ አስነስቷል፤ ትችትን ለማፈን በመሞከር በቀድሞው የአስተዳደር ስርአት ታግደው የነበሩትን ሚዲያዎች ላይ ይቀርብ የነበረውን የወንጀል ክስ አቋርጧል፡፡

እንዲሁም በዲያስፖራ ላይ የተመሰረቱ እንደ ኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ ያሉ ተቃዋሚ ሚዲያዎች  (OMN) እና የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) ወደ ሀገራቸው እንዲመጡ እና በህጋዊ መንገድ እንዲሰሩ ፈቃድ እንዲሰጣቸው መደረጉ አይዘነጋም።

እንደ ‘ካርድ’ ሪፖርት “በቀድሞው አገዛዝ ወደ እስር ቤት የተወረወሩ ጋዜጠኞችን ከእስር ተፈተዋል፤ ራሱን የቻለ የመገናኛ ብዙሀን ማህበርም እንዲመሰረት አድርጓል”።

ይሁን እንጂ ከጊዜያት በኋላ ግን “ከቀድሞ የባሰ የመብት እና የህግ ጥሰት እየተፈጸመ መሆኑን” ካርድ በጥናቱ አመላክቷል። አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎች ማህበር በተጨባጭ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ለማወቅ አዲስ ማለዳ ያደረገችው ጥረት ስልክ ባለማንሳታቸው ሳይሳካ ቀርቷል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here