በአዲስ አበባ ከተማ አራት ዋና ዋና የኮሪደር ልማት ግንባታዎች መጀመራቸውን ተከትሎ ነባር ይዞታዎች እየፈረሱ እና በአዲስ እየተተኩ ይገኛሉ። በተለይም በፒያሳ እና ሜክሲኮ በመሳሰሉ ጥንታዊ ህንጻዎች የሚገኙባቸው ስፍራዎች የሚከወኑ ፈረሳዎች ትችት ቢያስተናግዱም መንግስት “ማንም ያቦካው ጭቃ ሁሉ ቅርስ አይደለም” በማለት በፕሮጀክቱ ገፍቶበታል።
ፕሮጀክቱን የሚከውነው መንግስት እና “የልማቱ” ደጋፊዎች፤ ያረጁ መንደሮች ውብና ጽዱ አዲስ አበባን ለመፍጠር እንቅፋት ሆኗል፣ መንገዱም ጠቧል በማለት ፈርሶ እንደ አዲስ መገንባት አለበት ይላሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ከተማዋን ለመገንባት የሚካሄደው ፈረሳ ጥንታዊ እና ታሪካዊ ቦታዎችን በጥንታዊነት መዝግቦ እና ጠብቆ ማቆየት ሲቻል የማሕበረሰብ ትስስርና ታሪክን ማጥፋት አስፈላጊ አይደለም በማለት የሚከራከሩ አሉ።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርም ከሰሞኑን “ዝም ብለን የትውስት ነገሮችን ቅርስ እያልን በፍርድ ቤት በምናምን የሚያስተጓጉል አካሄድ መቀበልም፤ ማስተናገድ ተገቢ አይደለም” በማለት መንግስት ወደኋላ እንደማይል ፍንጭ ሰጥተዋል።
አዲስ ማለዳ በፒያሳ፣ አራት ኪሎ፣ መገናኛ፣ ሜክሲኮ፣ ወሎ ሠፈር እንዲሁም በሌሎችም የከተማዋ አካባቢዎች ነባር ቤቶች እና ህንጻዎች እየፈረሱ መሆኑን በተመለከተ የኪነ ሕንጻ ባለሞያዎች ማህበርን፣ የምጣኔ ሀብት እንዲሁም የፖለቲካ ባለሞያዎችን አነጋግራለች።
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የምጣኔ ሀብት ባለሞያ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት “በኮሪደር ልማቱ” 200 ሺህ ይሚሆኑ ነባር ይዞታዎችና ሱቆች እንደሚፈርሱ ግምታቸውን አስቀምጠዋል። በዚህ ስር መስተጋብር ፈጥረው የሚሰሩ ደላሎች፣ ጥበቃዎች፣ ጽዳት ሰራተኞች፣ ተቀጣሪ የምግብና መጠጥ አገልግሎት ሰጭዎችኝ ጨምሮ ከ500 ሺህ የሚበልጥ ሰዎች የፈረሳው ሰለባ እንደሚሆኑ ጠቅሰዋል። የእነዚህ ሰዎች ቤተሰቦቻቸውና ጥገኞቻቸው ሲቆጠሩ ደግሞ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ሕይወት ይነካል።
ፕሮጀክቱ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎችን ለአጭር ጊዜ አሊያም እስከመጨረሻው ስራ ያሳጣል የሚሉት የምጣኔ ሀብት ባለሞያው ማህበራዊ መሰረታቸው፣ ቤተሰባቸው የመፍረስ ዕድሉ ሰፊ በመሆኑ መፍትሔ የማይሰጣቸው ከሆነ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሰብዓዊ ቀውስ ይገጥማቸዋል ሲሉ አሳስበዋል።
ሌላኛው የምጣኔ ሀብት ባለሞያና ተመራማሪ ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ አንድ ፈረሳ ከመጀመሩ በፊት የኢኮኖሚ አዋጭነት፣ የፋይናንስ አዋጭነት እንዲሁም የሕብረተሰብ አዋጭነት ላይ ያተኮረ ጥናት እንደሚያስፈልግ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ጥናቱ የልማት ተነሺዎች ወደየት እንደሚነሱ፣ የስራ ሁኔታቸውን፣ ብዛታቸው፣ ህጻናት እና እናቶች ላይ የሚኖረው ተጽዕኖን ለመለየት ነው።
የሕግ ድንጋጌዎች
የአካባቢ ፈረሳን አስመልክቶ በ2011 ተሻሽሎ የፀደቀውና ይህ ጉዳይ በቀጥታ የሚመለከተው አዋጅ ቁጥር 1161/2011 በቀዳሚነት አንድ ይዞታ እንዲለቀቅ የሚደረገው ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ለሚሰራ ስራ ስለመሆኑ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ለህዝብ ኑሮ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አስተዋፅኦ ሲኖረው እንዲሁም ለአካባቢው የጎላ ማህበራዊ ፋይዳ ሲያበረክት እንደሆነ በአዋጁ ተመላክቷል።
በአዋጁ መሰረት አፍራሽ ግብረ ሃይሉ ፈረሳውን ከማካሄዱ ከአንድ ዓመት በፊት ነዋሪዎችን ማወያየት ይጠበቅበታል። የሚሰራው ሥራ አስቸኳይ ቢሆን እንኳን ነዋሪዎቹ ከመነሳታቸው ከስድስት ወራት በፊት ውይይት መደረግ እንዳለበት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያወጣው ደንብ ቁጥር 447/2012 አንቀጽ 4 ንዑስ አንቀፅ 5 ይደነግጋል።
በሕጉ መሠረት ማወያየት አስፈላጊ የሚሆንበት ምክንያትም ነዋሪው የሚለቀው ይዞታውን ብቻ ሳይሆን፣ ሃብቱን፣ ባህላዊ እና ማህበራዊ ትስስሩን እንዲሁም ታሪካዊ ትዝታውን ጭምር በመሆኑ ነው። በተመሳሳይም ከፈረሳው በኋላ አንድ ግለሰብ በተሰጠው ምትክ ቦታና ካሳ ላይ ቅሬታ ካለውና የተሰጠኝ ካሳ ተመጣጣኝ አይደለም ካለ ጉዳዩን በአንድ ወር ውስጥ ወደ ፍርድ ቤት መውሰድ የሚቻልበት አግባብ አለ።
የፈረሳው ማሕበራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ አንድምታ
ከአድዋ መታሰቢያ ሙዚየም ፊት ለፊት በተለምዶ የዶሮ ማነቂያ ከሚባለው ሰፈር እስካሁን 1 ሺህ 600 አካባቢ አባወራዎችን ማንሳቱን የአራዳ ክፍለ ከተማ መግለጹን አዲስ ማለዳ ለአብነት ተመልክታለች። ይሁን እንጂ የአካባቢው የልማት ተነሺዎች ከፍለ ከተማው በቅድሚያ ሰብስቦ የሦስት ወር ቀነ ገደብ እንደተሰጣቸው አሳውቆ አስር ቀን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የሦስት ቀናት ገደብ ሰጥተው እንዳፈረሱባቸው ቅሬታ አቅርበው ነበር።
የልማት ተነሺዎቹ የተሰጣቸው ምትክ ቦታ ቀድሞ ከነበሩበት የራቀ በመሆኑ ማህበራዊ ሕይወታቸውን እንደበተነው፣ የንግድ እና መኖሪያ ቤቶቻቸው መፍረሱን፣ ስራ ማቆማቸውን እና ማጣታቸውን፣ የቀን ገቢያቸው መቋረጡንም ገልጸዋል። እንዲሁም “እናቃወማለን ሰላማዊ ሰልፍ እንወጣለን ብላቹ እንዳታስቡ” በሚል ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው የሚገኙ እንዲሁም በርካታ ሰዎች በአንድ ስፍራ መሰብሰብ የማይችሉበት ሁኔታ መኖሩንም አዲስ ማለዳ ተረድታለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከሰሞኑ “ከታማኝ ግብር ከፋዮች” ጋር በነበራቸው ምክክር በአዲስ አበባ እየተካሄደ ስላለው ፈረሳ ምላሽ ሲሰጡ “አዲስ አበባ ላይ ትልቁ ድህነትና ችግር ያለው መሃከል ላይ ነው። መርካቶ፣ ፒያሳ፣ ሜክሲኮ የሚባለው ነው። ሲኤምሲ፣ ለቡ እንደዛ አይደለም። ዋናው ችግር ያለው መሀከል ነው፤ ዋናውን ችግር ደፍረን ካፈረስነው በአምስት ዓመት ከተማው ምን እንደሚመስል ታዩታላችሁ” ሲሉ ተደምጠዋል።
መሰረታዊ ዝግጅት የሚጎድለው ነው በማለት የማፍረስ ሂደቱን የሚቃወሙት የምጣኔ ሀብት ባለሞያው ፕሮፌሰር ዓለማየሁ የአገሪቱም ሆነ የአዲስ አበባ እቅድ ውስጥ ይኼ ነገር ፈጽሞ አልተካተተም ሲሉ ተችተዋል። እነዚህ ሰዎች ሃብታሞች ቢሆኑ ኖሮ መንግስት በቅድሚያ ያነጋግሯቸው ነበር የሚሉት ፕሮፌሰሩ፤ አንድም አካል ግን ውይይት ለማድረግ አለመሞከሩን አንስተዋል።
ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉ የተለያዩ ባለሞያዎች በዕቅድ ውስጥ አልነበረም ለሚለው ሃሳባቸው ከተሰሩ የወራት ዕድሜ እንኳን ያላስቆጠሩ አዳዲስ መንገዶችና ግንባታዎች እንዲሁም ገና በግንባታ ላይ የሚገኙ ቤቶች፣ ሱቆች እና መንገዶች መፍረሳቸውን እንደምክንያት ጠቅሰዋል።
“አሁንም የሚሰማን ባይኖርም” ቢያንስ ሰዎች በሚነሱባቸው ቦታዎች ላይ ቤት ተገንብቶ ቢሰጣቸው አሊያም በአንድ አካባቢ የነበሩ ሰዎችን በሌላ ስፍራም አንድ ላይ በማድረግ ማህበራዊ ትስስራቸው በማይፈርስበት ሁኔታ ማስፈር እንደሚገባ አሳስበዋል።
ምሁራን፣ ባለሞያዎች እንዲሁም የልማት ተነሺዎች ይኼን ቢሉም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተቃውሞዎችን አስተባብሏል። የሚፈርሱ አካባቢዎችን ቀድሞ ማሳወቁን እና ስብብሰባዎችም መደረጋቸውን የገለጸው የከተማ አስተዳደሩ “ስበሰባዎች ላይ ያለመገኘት አሊያም አያደርጉትም በሚል ለዘበተኛ ስሜት የተፈጠረ ክፈተት ነው” ብሏል።
የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ “ስድስት ጊዜ አወያይተናል። አንድም ጊዜ አንድም ሰው ልማቱን ተቃውሞ አስተያየት የሰጠን ሰው የለም” ብለው ምትክ የተሰጣቸው ሰዎች “ከነበሩበት የተሻለ ምቹ እና ጽዱ እንደየምርጫቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶችን እና የቀበሌ ቤቶችን” እንደተረከቡ ገልጸዋል።
በጉዳዩ ላይ ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ምክትል ሊቀ መንበር በቃሉ አጥናፉ ገዢው መንግስት ማህበራዊ እሴቶችን በማፍረስ እና በአዲስ መልክ በራሱ አምሳል ለመስራት መፍለጉ የፈረሳው ምክንያት እንደሆነ ገልጸዋል።
“ረጅም ጊዜ አብሮ የቆየ ማህበረሰብ በብዙ ማህበራዊ እሴቶች የተገነባ እንደመሆኑ አብሮ የመናበብ ሃይል ይኖረዋል። አሁን ግን መንግስት ማህበረሰቦች እንዳይናበቡ እያደረገ ነው” ሲሉ የተቹት የባልደራስ ምክትል ሊቀ መንበር መንግስት የስልጣን ዘመኑን ለማራዘም የሚጠቀምበት አንዱ መንገድ ማህበራዊ እሴቶችን ማፍረስ ነው ብለዋል። በተጨማሪም መንግስት መሬት በዙሪያው ላሉ ባለሃብቶች ሊሰጥ እንደሚችልም በቃሉ አጥናፉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
ማንነታቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ ፖለቲከኛ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ብልጽግና ፓርቲ በፖለቲካው አልተወከለም ከሚለው ኃይል ድጋፍ ለማግኘት “በአብዛኛው ከኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን፣ የአድዋ ድል አከባበር፣ ባንዲራ እንዲሁም ከሚኒሊክ ጋር በተገናኘ የሚሄድበት ፖሊሲ፤ ያንን ስርዓት በማዳከም አልተወከለም ላሉት ኃይል ይኼን አደረግንልህ” ለማለት የሚደረግ እንደሚመስል ገልጸዋል።
“ፈረሳው ፖለቲካዊ አንድምታ ግን የለውም ብዬ መከራከር አልችልም” የሚሉት ፖለቲከኛው “መንግስት አዲስ አበባ ላይ ይኼን ሲያደርግ ኦሮሚያ ላይ ውጤት ይፈልጋል። ይኼውም ብዛት ካለው አካባቢ ድምጽ ለማግኘት የሚያስችለው ይሆናል” ብለዋል።
አንጋፋው የምጣኔ ሀብት ባለሞያ ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገዳ የኢኮኖሚ፣ የፋይናንስ እና የማሕበረሰብ አዋጭነት ታሳቢ ያልተደረገበት ፈረሳ በመሆኑ ይኼ “ኢኮኖሚያዊ ሳይሆን ፖለቲካዊ ፈረሳ ነው” ሲሉ ተችተዋል።
የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የአዲስ አበባ ከተማ የኮሪደር ልማት ስራን ከሚያስፈጽሙ አመራሮች እና የስራ ኃላፊዎች ጋር በፕሮጀክቱ ዙሪያ ባደረጉት ውይይት ላይ የስነ ህዝብ አወቃቀር (Demography) ለመቀየር ነው የሚለውን ሃሳብ አስተባብለዋል። “አዲስ አበባ ውስጥ ከበቂ በላይ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ እና ሌሎችም በርካታ ብሔሮች አሉ። የሌለው ኖሮ ለማምጣት የምንቸገርበት አይደለም” ሲሉም ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ግን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ከቀናት በፊት በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው “ከዚች አገር ታሪካዊ ሂደት ጀምሮ የኦሮሞ ህዝብ ከከተማው እየሸሸ ነው”ብለው በከተሞች የህዝቡን ባህላዊ፣ የባህል አብዮት፣ ፖለቲካ እና ሶሻሊዝም ለማጠናከር አበባ ላይ ትላልቅ ፕሮጀክቶች በሂደት ላይ መሆናቸውን በጠቆሙ ማግስት ነው።
በሌላ በኩል ግን የኮሪደር ልማት ስራው ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታና እሴት ከመፍጠር አኳያ ከታየ ጽዱ፣ አረንጓዴ፣ የእግረኛና የብስክሌት መጓጓዣ ያለው መንገድ ከመገንባት አንጻር መልካም እንደሆነ ተገልጿል። ከዚያ ባለፈ ግን የከተማ ውስጥ መንገድ በመሆኑ ምርት የማይመረትበት እና ምርት የማይጓጓዝበት የከተማ ጌጥ ከመሆን አይዘልም ሲሉ ሌላ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ባለሞያ ገልጸዋል።
አክለውም “የእለት እንጀራውን ለሚያጣ ዜጋ ጽዱና አረንጓዴ መንገድ የተቀናጀና ሰብዓዊ ልማት ካላመጣለት መንገዱ ብቻውን ፋይዳ አይኖረውም” ሲሉ አጽንዖት ሰጥተዋል።
ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት ፖለቲከኛ አዲስ አበባ ውስጥ የሕዝብ ቁጥር፣ የኑሮ ውድነት እና የተሽከርካሪ ፍሰትን መቆጣጠር ትኩረት ይፈልጋሉ ብለው እየተከናወነ ያለው ፈረሳ በከተማዋ የትራፊክ ፍሰቱን ለማስተካከል ከሆነ ይበል የሚያሰኝ ነው ይላሉ።
ፈረሳው እና ምጣኔ ሀብታዊ አንደምታው
ሃሳባቸው ለአዲስ ማለዳ ያጋሩ አንድ የምጣኔ ሀብት ባለሞያ የመንገዱ ግንባታ የሚጠይቀው አቅርቦት በቢሊየኖች የሚቆጠር ብር ስለሆነ አዲስ ፍላጎት በመቀስቀስ ወትሮውንም እጥረት የነበረባቸውን እንደ ሲሚንቶ፣ ብረት፣ ድንጋይ፣ ጠጠርና አሸዋ የመሳሰሉት ላይ እጠርት እና ከፍተኛ የዋጋ ንረት ሊያስከትል እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ዘመቻው ሱሪ በአንገት ነው የሚሉት ባለሞያዎቹ ማንኛውም መጠነ ሰፊ ማፈናቀልና በጀት የሚጠይቅ ፕሮጀክት ላይ መቼ? በማን? እንዴት? ለምን ? የሚሉት ጥያቄዎች በአግባቡ መልስ ባላገኙበትና የሕዝብ ንቁ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ባልተካተተበት ሁኔታ በጥድፊያ እና በቀጭን ትዕዛዝ የሚተገበር ከሆነ ጥያቄ ላይ መውደቁና መጠላቱ አይቀሬ ነው ይላሉ።
አዲስ አበባን “ውብና ጽዱ ከተማ እናደርጋታለን” በሚል የተጀመረዘው ዘመቻ አሁን ባለው ነባራዊ የሰላም እጦት፣ የኑሮ ውድነት፣ ከውጭ አገራት ጋር ያለ ግንኙነት መሻከር ጋር ተደማምሮ ወትሮም ጫናው የከበደውን ሕብረትሰብ ዳግም ብዙዎችን ከቤት ንብረታቸው ያፈናቀለ፣ ማህበራዊ ትስስሮችን የበጠሰ፣ በርካቶችን ከነበሩበት የኑሮ ደረጃ ዝቅ የሚያደርግ እንዲሁም ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያ እና ሰብዓዊ ቀውስ የሚያመጣ ነው ሲሉ በርካቶች ይደመጣሉ።
ምንም እንኳን የኮሪደር ልማት ግንባታው በከተማ አስተዳደሩ ቢሆንም አገሪቱ ያለችበት የኢኮኖሚ ችግር አገር አቀፍ በመሆኑ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ስለመሆኑም ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉ አካላት ጠይቀዋል።
ማጠቃለያ
አዲስ ማለዳ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥላ ስር የሚገኘውን የኢትዮጵያ አርክቴክቸር ህንጻ ኮንስትራክሽንና ከተማ ልማት ተቋም ሃሳብ ለማካተት ያደረገችው ሙከራ “እኛ ምንም ማለት አንችልም። ማንን መጠየቅ እንዳለብን ግራ ገብቶናል” በሚል ምላሻቸው ሳይሳካ ቀርቷል።
ከዚህ ቀደም ከአዲስ ማለዳ እህት ሕትመት ኢትዮጵያን ቢዝነስ ሪቪው ጋር ቆይታ ያደረጉት የተቋሙ ሊቀ መንበር ፋሲል ጊዮርጊስ “እነዚህ ህንጻዎች ምን ዋጋ እንዳላቸው እና ሳይፈርሱ እንዴት ጥቅም ላይ ማዋል የሚችሉበት መንገድና ዕውቀት ስሌላቸው ማፍረሱን ይመርጣሉ” ብለው ነበር።
በመሆኑም በከተማዋ የሚገኙ ጥንታዊ ህንጻዎችን መጠበቅ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ በመሆኑ እነዚህን ቅርሶች መጠበቅ የሚያስችል ፖሊሲዎችን ተግባራዊ ማድረግ ተገቢ ነው ይላሉ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደሩ በበኩሉ የመንገድ ኮሪደር ልማት ስራና የስማርት ሲቲ ግንባታ ጋር ተያይዞ በልማት ምክንያት ለተነሱ የግል ይዞታ ለነበራቸው ነዋሪዎች በመሬት አስተዳደር የካሳ መመሪያ በ79/2014 መሰረት ማስረከቡን የገለጸ ሲሆን
በበርካታ አካባቢዎች ከአንድ ዓመት አሊያም የስድስት ወር ዕድሜ ሳይሰጣቸው ከአስር ቀናት እስከ 12 ሰዓታት የጊዜ ገደብ ብቻ በመስጠት ፈረሳው ተካሂዷል፤ እየተካሄደም ይገኛል።
ማንም ሰው ጥቅሙና መብቱ ከተከበረ ልማትን አይጠላም የሚሉት የተለያዩ ባለሞያዎች የሰው ልጅ ለማዳ በመሆኑ ጊዜ የሚሰጥና የኢኮኖሚ ጥቅሙን ያስጠበቀ እድል ካገኘ ይላመዳል ሲሉ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።


