ሜቴክ 6.5 ሚልየን ብር እንዲከፍለኝ ብከስም፤ ጭራሽ 1.5 ሚልየን ብር እንድከፍል ተፈርዶብኛል- ቅሬታ

0
1282

“ፍትህ በስልጣን ተሸፍናለች” ሲል ቅሬታውን ለአዲስ ማለዳ ያቀረበው እሱባለው ተካልኝ፤ በቀድሞ መጠሪያ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) አሁን ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ከተባለው ተቋም ያልተከፈውን 6.5 ሚልየን ብር በፍርድ ቤት ቢጠይቅም ፍርድ ቤቱ 1.5 ሚልየን ብር ለድርጅቱ እንዲከፍል ተፈርዶብኛል ብሏል። 

ከ8 አመታትን በላይ በቀድሞ ስሙ ሜቶክ አሁን ኢትዮ ኢንጂነሪን ግሩፕ እና በእሱባለው ተካልኝ መካከል የቆየው የችሎት ሂደት “ፍትህ በተጓደለበት መልኩ” ውሳኔ እንደተሰጠበት ግለሰቡ ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል። 

እሱባለው በ2006 በማህበር መደራጃ መመሪያ መሰረት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ውሃ ማረፊያ ቦታን ለማጽዳት (ደን ለመመንጠር) ከቀድሞው ሜቴክ ኩባንያ ጋር በገባው ውል መሰረት 1 ሺህ 137 ሄክታር መሬት መንጥረው እንዳስረከቡ ይናገራል። 

“ስራ ስንጀምር የመለኪያው መሳሪያ ሜትር ወይስ ዲጂታል የመሬት መለኪያ ጂ.ፒ.ኤስ ይሁን የሚል ክርክር ተነስቶ፤ 12 ሄክታር ተዳፋት ቦታ በናሙናነት ተወስዶ በሜትርና በዲጂታል መለኪያው ሲለካ ጂ.ፒ.ኤስ የሜትሩን መጠን በግማሽ ያህል ስለቀነሰ እና ከሜዳማ ቦታ በስተቀር ተዳፋትና ተራራማ ቦታ ለመለካት ትክክለኛ የቆዳ ስፋት እንደማይሰጥ በጋራ አረጋግጠን በሜትር እንደሚለካ ተስማምተን በመስራት ሶስት ጊዜ በሜትር ተለክቶልን ሶስት ጊዜ ክፍያ ተቀብለን ስምምነቱን ተግባራዊ አድርገነዋል” ሲል እሱባለው አብራርቷል። ጂ.ፒ.ኤስ የሞባይል ቀፎ መሰል መሳሪያ ሲሆን ከመነሻው እስከመድረሻው ይዘውት በመሄድ ወጣ ገባ የሌለው መሬትን ብቻ የሚለካ ነው።

በስምምነታቸው መሰረት በ1 ሄክታር መሬት ከ8 እስከ 13 ሺህ ብር ክፍያ የተስማሙ ሲሆን ለ1 ሺህ 137 ሄክታር መሬት በአጠቃላይ 14.5 ሚሊዮን ብር ክፍያ ለእሱባለውና አብረውት ለተደራጁት ሊከፈል ነው። ይሁን እንጂ “ስራውን አስረክበን ከቦታው ከወጣን በኋላ በሶስተኛ ዙር የክፍያ ሰርተፍኬት ላይ 70 በመቶ ወይም 6.5ሚሊየን ብር ያህል ክፍያ ስላልተከፈለን እንዲከፈለን ስንጠይቅ” የቀድሞ የሜቴክ ባለስልጣናት ባልታወቀ ምክንያት “እልህ ተጋብተው ድጋሚ በጂ.ፒ.ኤስ ለክተን ካልሆነ በሜትር በተለካው አንከፍልም” ማለተቸውን እሱባለው ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበረው ቆይታ ገልጿል። 

የኢትዮጵያ ብረታ ብረት እና ኢነጅነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ዋና ዳይሬክተር የነበሩት እና በ2011 ሕዳር ወር በቁጥጥር ስር ውለው ከሁለት ሳምንታት በፊት ክሳቸው የተቋረጠው ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው ጉዳዩን ይዘውት እንደነበረ አዲስ ማለዳ ማወቅ ችላለች።

ክፍያውን ካለመፈጸም ባለፈ “ሱሪ የታጠቀ ሚኒስተር ሲያስከፍለኝ እናያለን” ሲሉ በመዛታቸው ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስደው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ቀሪ ክፍያቸውን ጠይቀዋል። አዲስ ማለዳ ከቅሬታ አቅራቢው እንደተረዳችው ከጀነራል ክንፈ ዳኘው መታሰር በኋላ ጉዳዩን የድርጅቱ የሕግ ባለሙያዎች ይዘውት ቆይተዋል። 

ነገር ግን ሜቴክ ከሳሽ እሱባለው ተካልኝ ባልተገኘበት ቦታው በድጋሚ በጂ.ፒ.ኤስ የተለካ ነው የተባለ በሜትር 1 ሺህ 137 ሄክታር የነበረውን 577 ሄክታር ብቻ እንደሆነ ተደርጎ የተዘጋጀ እና የከሳሽ ፊርማ የሌለበት ሰነድ ለፍርድ ቤት በማቅረብ፤ ተከሳሽ እንኳን ቀሪ ክፍያ ሊከፈላቸው ቀርቶ እንደውም ከሳሽ ቀድሞ ከተከፈለው ክፍያ ትርፍ የመንግስት ገንዘብ ሊመልሱ ይገባል በማለት ከሳሽ ሆነው መቅረባቸውን እሱባለው ተናግሯል።

በስምምነታቸው መሰረት የቀደሙት ሶስት ክፍያዎች በሜትር መለኪያ መከፈሉን የሚያሳይ የክፍያ ሰርተፍኬት ፍርድ ቤቱ መሠረታዊውን የፍርድ ነጥብ ሳይይዝ ያለ ምንም ማስተባበያ ወደጎን መተውን ቅሬታ አቅራቢው አመላክቷል።

አዲስ ማለዳ በቀድሞ አጠራሩ ሜቴክ የአሁኑ ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ምላሽን ለማካተት ያደረገችው ተደጋጋሚ ጥረት መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል። 

እንደ እሱባለው ገለጻ የሜትር መለኪያ መሳሪያ ትክክለኛነቱ በክርክር ሂደት በማስረጃ ማጣራት የማያስፈልገው እውነታ ሆኖ እያለ ተገቢውን የክርክር አመራር ስርዓት ሳይከተል ባለስልጣናቱን ለመጥቀም ፖለቲካዊ ውሳኔ ለመስጠት እንዲቻል አዲስ ማስረጃ ለማፈላለግ ቦታው በሜትር ቢለካ ይሻላል ወይስ በጂ.ፒ.ኤስ የሚለው የባለሙያ ማብራሪያ እንዲሰጥበት ለኢትዮጵያ ካርታ ስራ ኤጀንሲ “ሕገ ወጥ” ትዕዛዝ ተሰጥቷል። 

የኢትዮጵያ ካርታ ስራ ኤጀንሲ “የሜቴክ የቀድሞ ባለስልጣናትን ተጽእኖ ተቋቁሞ ጂ.ፒ.ኤስ በሜዳማ ቦታ ላይ ትክክለኛ የቆዳ ስፋት መጠን ሊሰጠን ይችላል ነገር ግን ተዳፋትና ተራራማ ቦታዎች አካተን የምንለካ ከሆነ ጂ.ፒ.ኤስ ትክክለኛ የቆዳ ስፋት አይሰጠንም፤ እደዚህ አይነት ቦታ በሜትር በመለካት ትክክለኛውን የቆዳ ስፋት ማወቅ ይቻላል ሲል” ምላሽ እንደሰጠ ተገልጿል። 

በመሀል ችግሩን በሽምግልና ለመፍታት በተደረገ ሙከራ በሜቴክ በኩል ያሉ ወገኖች የጂ.ፒ.ኤስ መለኪያ ትክክል አይደለም ብለው ስላመኑ የሽምግልና ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ ሪፖርት አድርል ሲል እሱባለው ተናግሯል። ፍርድ ቤቱም ከሳሽ እና ተከሳሽ በተገኙበት ቦታው በድጋሚ በሜትር እንዲለካ ለኢትዮጵያ ካርታ ስራ ኤጀንሲ ትእዛዝ ሰጥቶ ነበር። 

የቀድሞው ሜቴክ ኃላፊዎች ግን በማይፈልጉት መንገድ መለካት ሲጀመር፤ “ሆን ብለው ወሰን በማመላከት ክርክር እና አለመግባባት ፈጥረው የሜትር ልኬቱ እንዲቋረጥ ተደርጎ ሌላ ባለሙያ እንዲቀየር እና የኢትየዮጵያ ኮንስትራክሽን ዲዛይን እና ሱፐር ቪዥን ስራዎች ድርጅት እንዲመደብ” በድርጅቱ ጠበቃ በኩል ጠይቀዋል። 

በዚህም ፍርድ ቤቱ ግራ ቀኙ በወሰኑ “ቢስማሙም ባይስማሙም ቦታው ከሜትር ውጭ በሆነ የመለኪያ መሳሪያ በመጠቀምም ቢሆን” ተለክቶ እንዲቀርብ ድጋሚ “ሕገ ወጥ” ትዕዛዝ ተሰጥቷል ተብሏል። የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን  ዲዛይንና ሱፐር ቪዥን ስራዎች መስሪያ ቤት “የሜቴክን የቀድሞ ባለስልጣናት ተጽእኖ መቋቋም አልቻልም” ሲል እሱባለው ቅሬታውን ለአዲስ ማለዳ አስረድቷል። 

በድጋሜ ከሳሽ እሱባለው በቦታው ባልተገኘበት ተከሳሽ ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ (የቀድሞው ሜቴክ) ብቻ የሚያሳየውን ቦታ ከሜትር ውጭ በሆነ የመለኪያ መሳሪያ በመጠቀም በሜትር 1 ሺህ 137 ሄክታር የነበረው በጂ.ፒ.ኤስ 577 ሄክታር የተባለውንም በመቀነስ የ533 ሄክታር ሰነድ ለፍርድ ቤት ማቅረባቸው ተመላክቷል። እሱባለው እንደሚለው “ድጋሜ መለካት አስፈላጊ ከሆነ እንኳን ከሳሾች በሌሉበት መለካት ሕገ ወጥ ነው”።

ቀጥሎም ፍርድ ቤቱ የካርታ ኤጄንሲ ባለሙያዎች “የሜትር መለኪያ ካልሆነ በስተቀር ጂ.ፒ.ኤስ አግባብነት ያለው መለኪያ አይደለም” ማለታቸውን  ግምት ውስጥ ሳያስገባ ከሳሽ የክፍያ ሰርተፍኬት መያዙ ብቻ ስራ ስለመስራቱ ማረጋገጫ አይደለም በማለት የክፍያ ሰርተፍኬቱንም ውድቅ አድርጎታል። 

“ባለሙያዎቹ 533 ሄክታር መጠን ቢለኩትም ተከሳሽ በጂ.ፒ.ኤስ 577 ሄክታር እንደተሰራ ስላመነ በጂ.ፒ.ኤስ ልኬት መሰረት ከሳሽ [እሱባለው ተካልኝ] ለተከሳሽ ድርጅት [የቀድሞ ሜቴክ] 1 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር ይክፈሉ ሲል ሕገ ወጥ” ውሳኔ ተሰጥቷል ሲል እሱባለው ኮንኗል።

ቀሪ ክፍያ ለመጠየቅ የተጀመረው ክስ ተገልብጦ ከሳሽ ጥፋተኛ በማድረግ በተወሰነው ውሳኔ ላይ እሱባለው ይግባኝ ጠይቆ የነበረ ሲሆን ስለሆነም በጥር 16 ቀን 2016 የተፈጸመ የሕግ ስህተት የለም የሚል ውሳኔ ፍርድ ቤቱ እንዳስተላለፈ እሱባለው ቅሬታውን ለአዲስ ማለዳ ገልጿል። 

“በፍትህ አደባባይ ፍትህ አጥተናል። ከእኔ በታች ሲሰሩ የነበሩት ሰራተኞችም የሰራንበትን ክፈለን እያሉ በተለያየ መንገድ እየጠየቁኝ ነው። እኔ ደግሞ የሰራሁበትን ስጠይቅ የባሰ ባለ እዳ ሆኜ ተመልሻለሁ” ሲል ጉዳዩን ለአዲስ ማለዳ አስረድቷል።

ከዓመታት በፊት የምንጣሮ ስራ እንዲያከናውኑ ስምምነት የፈረሙ 160 ማህበራት 340 ሚሊየን ብር ሊከፈላቸው ሲገባ ሜቴክ ገንዘብ ከልክሎናል ማለታቸው አይዘነጋም። በተጨማሪም ሜቴክ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በገባው ውልም ከ1.9 ቢልየን ብር በላይ በማጭበርበር 50 የሚደርሱ ተጠርጣሪዎች መከሰሳቸ አይዘነጋም። 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here