የገቢዎች ሚኒስቴር በኅዳር ወር 18.3 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 19.2 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን ገለፀ።
የወሩ ክንዉን ካለፈዉ ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በብር የ5.97 ቢሊዮን ወይም 36.14 በመቶ አብላጫ ያለው ነው። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባለፉት አራት ወራት ከ90 ቢሊዮን ብር (100.8 በመቶ) በላይ ገቢ መሰብሰቡን እና በ2012 በጀት ዓመት የአራት ወራት ክንዉን ከባለፈዉ ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ሲነፃፀር የ21 ቢሊዮን ብር ብልጫ ያለዉ፣ የ31 በመቶ እድገት ያስመዘገበ እንደነበር ይታወሳል።
ባለፈዉ የጥቅምት ወር 33.44 ቢሊዮን ታቅዶ 32.67 ቢሊዮን መሰብሰቡ ተጨማምሮ፣ በአጠቃላይ ከሐምሌ ጀምሮ እያስመዘገበ ያለዉ የገቢ አሰባሰብ ውጤት ስኬታማ መሆኑ የዓመቱን እቅድ ለማሳካት ማሳያዎች እንደሚሆኑ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አስታውቋል።
በ2011 ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በሠራቸዉ የንቅናቄ ሥራዎች በአጠቃላይ በአገር አቀፍ ደረጃ በተፈጠረዉ ግንዛቤ የገቢ አሰባሰብ ከመቼዉም ጊዜ በላይ በተሻለ መልኩ እድገት እያሳየ መምጣቱ እና ከኢኮኖሚ ማደግ ባሻገር የግብር አሰራር መሻሻል እንደሚያስመዘግብ ተገልጿል።
የግብር አሰባሰብ ስርዓቱን በዘመናዊ መንገድ ለማከናወን በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። ከእነዚህም ውስጥ በፌዴራል ገቢዎች ሚኒስቴር ግብር ከፋዮች መካከል እስከ አሁን 4ሺሕ671 ግብር ከፋዮች በበይነ መረብ የሚያሳውቁ ሲሆን፣ እነርሱን ጨምሮ ዐስር ሺሕ ግብር ከፋዮችን ወደ ዘመናዊዉ የበይነ መረብ ማህደር ግብር ክፍያ ስርዓት ለማስገባት እየተሠራ ይገኛል ተብሏል።
ቅጽ 2 ቁጥር 58 ታኅሣሥ 4 2012



