በስርቆት የተጠረጠሩ አራት የመድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ሠራተኞች በቁጥጥር ስር ዋሉ

0
513

እስከ አሁን መጥፋቱ የተረጋገጠ መድኃኒት የለም – ኤጀንሲው

ከኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ዋና መሥሪያ ቤት መጋዘን ከኹለት ሳምንታት በፊት መድኃኒቶችን ሰርቀዋል ተብለው የተጠረጠሩ አራት የድርጅቱ ሠራተኞች ለሕግ ተላልፈው ተሰጡ።
በኅዳር ወር መጨረሻ መድኃኒቶቹ ከኤጀንሲው መጋዘን መጥፋታቸው የሚገመት ሲሆን፣ በኤጀንሲው መጋዘን ውስጥ የሚሠራ ግለሰብ የመድኃኒቶቹን መጥፋት ማሳወቁን ተከትሎ የሚጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራው እንደተጀመረ ታውቋል።
ተጠርጣሪዎቹንም ለመለየት በመጋዘን ውስጥ ያሉ የደኅንነት ካሜራዎች ጥቅም ላይ ውለዋል። ይህንንም ተከትሎ መድኃኒቶቹ መጥፋታቸው በሚገመትበት ዕለት ከኤጀንሲው ግቢ የወጣ ተሽከርካሪ ሹፌር ጋር በስልክ ለመገናኘት ጥረት ቢደረግም፣ አሽከርካሪው መኪናውን አዲስ አባባ ውስጥ ከሚገኙ የኤጀንሲው ቅርንጫፎች በአንዱ ውስጥ በማቆም መጥፋቱ ታውቋል።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሎኮ አብርሃም በጽሑፍ መልዕክት ለአዲስ ማለዳ በሰጡት ምላሽ፣ መሥሪያ ቤታቸው ግቢ ውስጥ የተባለው ዝርፊያ አልተፈፀመም ብለው ካስተባበሉ በኋላ፣ ‹‹በደኅንነት ካሜራ ዕይታ መሠረት የተጠረጠሩ አራት ግለሰቦች ላይ ምርመራ እያደረግን ነው፤ ነገር ግን እስከ አሁን መጥፋቱ የተረጋገጠ መድኃኒት የለም›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የድርጅቱ ሠራተኞች በዋና መሥሪያ ቤቱ እንዲህ ዓይነት ስርቆቶች የተለመዱ እንዳልሆኑ ገልጸው፣ በቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት መጋዘኖች ግን በጣም የተለመደ ድርጊት እንደሆነ ተናግረዋል።
ይህንን ያስተባበሉት ዋና ዳይሬክተሩ ባለፉት አራት ዓመታት ከየትኛውም ቅርንጫፍ እንደዚህ ዓይነት ድርጊት ሪፖርት ተደርጎ እንደማያውቅ፣ ነገር ግን በዋናው መሥሪያ ቤት የተከሰቱ ኹለት ጉዳዮች በሕግ ተይዘው በፍርድ ቤት በመታየት ላይ መሆናቸውን ገለፀው፣ ከእነዚህ ውጪ ግን ሌላ የተከሰተ ነገር የለም ብለዋል።
አዲስ ማለዳ ከኤጀንሲው ማረጋገጥ ባትችልም፣ በኤጀንሲው ያሉ ምንጮቿ እንደገለፁት ሐሙስ ታኅሳስ 03/2012 ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን እስከ አሁን ያልተያዙ ተጠርጣሪዎች መኖራቸውም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ በ2011 የበጀት ዓመት 16 ቢሊዮን ብር ያህል መድኃኒቶችን የገዛ ሲሆን፣ ከዚህ ገንዘብ ውስጥ ከ85 በመቶ በላዩ ከውጭ ለጋሾች የሚገኝ ነው። የአገር ውስጥ መድኃኒት አምራቾች በጣም አነስተኛ መጠን ያለው ምርት ያቀርባሉ። ለዚህም የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለዝቅተኛ አቅርቦታቸውም ሆነ አፈጻጸማቸው እንደ ምክንያት ይነሳል።

ቅጽ 2 ቁጥር 58 ታኅሣሥ 4 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here