ሳምንቱ ኢትዮጵያ በመገናኛ ብዙኀን እንዲሁም በዓለም ትላልቅ በሚባሉ መድረኮች ላይ ሥሟ በተደጋጋሚና በትልቅነት የተነሳበት ነው። ቤተልሔም ነጋሽ ይህን ክስተት መነሻ አድርገው ይልቁንም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) በኦስሎ የኖቤል የሰላም ሽልማታቸውን መቀበላቸውን ተከትሎ፣ በዓለም ፊት የተገለጠውን የኢትዮጵያን ክብር አንስተዋል። ከአገር ውስጥ እስከ ባሕር ማዶ በዚህ ላይ የተነሱ ድጋፎችንና ተቃዉሞዎችንም ቃኝተውም፤ በሆነው ሁሉ አስተያየት ከመስጠት አልፈን ለተሻለ ነገ ብንሠራስ ብለዋል።
ያለፈው ሳምንት ኢትዮያውያን በተለያዩ ዓለም ዐቀፍ መድረኮች ዕውቅናን ያገኙበት፣ የተሸለሙበት፣ ሥማችን በበጎ የተነሳበት ነበር። ከተሸላማቻችን መካከል የኖቤል የሰላም ሽልማታቸውን ባለፈው ማክሰኞ የተቀበሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና በወር አበባ ንጽህና ዙሪያ በተለይ ለታዳጊ ሴቶች ዳግም ጥቅም ላይ የሚውል የንጽህና መጠበቂያ በመሥራትና በፈጠራ በማስመዝገብ 750 ሺሕ ሴቶችን የሥራ ዕድል በመፍጠር ጭምር ላደረገችው አስተዋጽኦ፣ የሲ ኤን ኤን የዓመቱ ጀግኒት ተብላ የተመረጠችው ፍሬወይኒ መብራህቱ ዋነኞቹ ናቸው። በዓለም ፊት በተለይ በመገናኛ ብዙኃኑ መጥፎ እንጂ ጥሩ ከአፍሪካ አይወጣም እስኪባል፣ ከሩጫ በቀር በጎ ታሪክ የሌለን ሰዎች በጎ ዜና እንዳለንም ለዓለም የታየንበት ሳምንት ሆኖ አልፏል።
የሳምንቱ ታላቅ ክስተት የነበረውን የጠቅላይ ሚኒስትሩን የሽልማት አቀባበል ሥነ ሥርዓት ዘርዝረን ብናይ፤
“ኦስሎ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ እስክትመስል ድረስ በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማና በኢትዮጵያ ባነሮች ተውባ ሰነበተች። ሚዲያዎች ሁሉ ስለ ኢትዮጵያ በኩራት መሰከሩ። ኢትዮጵያን በድህነትና በጦርነት፣ በረሐብና በእልቂት የሚያውቋት ሁሉ አዲስ ታሪክ ሆነባቸው። በሩጫ ስናሸንፍ ነበር የሚያውቁን፤ ዛሬ ደግሞ በሰላም ሥራችን በዓለም አቀፍ መድረክ ስናሸንፍ አዩን። ከግሪን ላንድ እስከ ኒውዚላንድ፣ ከቺሊ እስከ ጃፓን ዓይኖች ሁሉ ወደ ኦስሎ ተተክለው ስለ ኢትዮጵያ ተመለከቱ።
በመላው ዓለም ተበትነው የሚኖሩት ኢትዮጵያውያን የዜግነት ክብራቸውን ከፍ የሚያደርግ ሥራ በታሪክ ውስጥ ሲመዘገብ አዩ። ልጆቻቸው በባዕድ ሀገር በታሪካቸው ኮሩ። አገራቸው በምሳሌነትና በአርአያነት ስትነሳ በዓይናቸው ብሌን ተመለከቱ፤ በጆሮአቸው ሰሙ። በዓረብ አገር የሚኖሩ ዜጎቻችን አሠሪዎቻቸው ወደታች ሳይሆን ወደላይ እንዲዩዋቸው የሚያደርግ ታሪክ በዓለም አደባባይ ሲከወን ዕንባ በተሞሉ ዓይኖቻቸው አደነቁ።
ኹለት ዓይነት ታሪክ ሲሠራ የዓለም ዓይኖች ታዘቡ። በጦርነት የምትታወቅ ሀገር የሰላም ሽልማት ተሸለመች። የሰላምን ዋጋ የሚያውቀው ዓለም፤ የሰላም ሽልማት በቀላሉ እንደማይገኝ የሚያውቁ የዓለም ዜጎች በደስታና በክብር አብረውን ከረሙ። ለሕዝቦች መቀራረብ፣ ለሕዝቦች መገናኘት፣ ለሕዝቦች ዕርቅና ሰላም መሥራት የሚያሸልም ተግባር መሆኑን የሚያውቁ ሁሉ፤ የቻሉ በኦስሎ ጎዳናዎች ተገኝተው፤ ያልቻሉ በየቴሌቭዥን መስኮቶች አፍጥጠው ክብር ሰጡን።
በኦስሎ ያገኘነው ክብር የአገራችን ጉዞ ከትናንት የዛሬው፣ ከዛሬውም የነገው እጅግ የተሻለ መሆኑን አመላክቶናል። ይህ ለኢትዮጵያውያን የመጀመሪያ እንጂ የመጨረሻ አይሆንም። በሰላም፣ በሳይንስ፣ በሥነ ጽሑፍ ገና ብዙ ኢትዮጵያውያን ወደ ኖቤል አገር ወደ ኖርዌይ ይመጣሉ።
ዛሬ ያገኘነውን አክብረን አያሌ ኢትዮጵያውያን በዓለም አቀፍ መድረኮች ሀገራቸውን እንዲያስጠሩ እንሠራለን። ለዚህ ደግሞ ሁላችንም ሀገር የሚያስጠራ ጥረት እንድናደርግ ጥሪ አቀርባለሁ። “
ከላይ የተዘረዘረው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሰላም የኖቤል ሽልማት መረከባቸውን አስመልክተው በፌስቡክ ገፃቸው በሽልማቱ ማግስት ያስተላለፉት መልዕክት ነው።
የሆነ ሆኖ ዜናው ለአገራችን በጎ ገጽታ ትልቅ አበርክቶት ያለው መሆኑ ተረስቶ ዋጋ እንዳለው ጉዳይ የዋጋውን ያህል ሳይሆን በኹለቱም ወገን (በደጋፊም በተቃዋሚም) አላግባብ ተለጥጦ ታይቷል። ከተቃዋሚው ጎራ በሽልማቱ ወቅት ካደረጉት ንግግር፣ ‹ቋንቋ እናውቃለን!› ባዮች ትችት እስከ ‹ሸምድደው ነው ያወሩት!› ተራ ግምት፤ በደጋፊዎች ሽልማቱን የመጨረሻው የብቃት መለኪያ አድርጎ እስከማየት የደረሰ ነው።
እውነታው ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ይህ ቀን ለኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪካ ታሪካዊ ቀን ነው:: በበሽታ በረሃብ በእርስ በርስ ጦርነት የሚያውቀን ዓለም ቢያንስ ሰሞኑን ሥማችንን በበጎ አንስቷል። አማርኛ ቋንቋችን ኖቤል የክብር መዝገብ ላይ ተፅፎበታል፤ ዘፈኖቻችን ኖቤል መድረክ ላይ ተዘፍነዋል። እንኳን ደስ አለን!
ለታዘበው ሰው የኖቤል ኮሚቴዋ ከሽልማቱ በፊት ስታወራ ስለ እኛ አይመስልም። ሥማችንን በመልካም ገድል ሲነሳ፣ የሰው ዘር መገኛ፣ በቅኝ ያልተገዛች፣ የአፍሪካ መዲና ስንባል እንባው የማይመጣ ካለ ደረቅ ነው ብቻ ሳይሆን ይህቺን አገር ይወዳል? የሚለውን ጥያቄ ያጭራል። ከዚያም አልፎ ግድ የለም ተስፋ አለን ያስብላል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ደግሞ ወደድንም ጠላንም ተስፋችንን የመለሱ ሰው ናቸው!
ለዕለቱ ብዙ ከሚያሳስበን ጉዳይ አረፍ ብለን በኢትዮጵያዊነታችን ስንኮራ ብዙ ተግዳሮቶች ያሉን መሆናችንንም አንዘነጋም። የኖቤል የሰላም ኮሚቴ ሊቀመንበር ቤሪት ሬይሳ አንደርሰን በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንዳሉት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ባስመዘገቧቸው ሦስት ዋና ዋና ውጤቶች የ2019 የኖቤል ሰላም ተሸላሚ እንዲሆኑ ተመርጠዋል።
እነዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተለይ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ለዓመታት የዘለቀውን ውዝግብ በሰላም ለመፍታት ባሳዩት ተነሳሽነት፣ በኢትዮጵያ በዴሞክራሲ ግንባታ ለተጫወቱት ሚና እንዲሁም በኢትዮጵያ፣ በምሥራቅና በሰሜን ምሥራቅ አፍሪካ ሰላምና እርቅ እንዲመጣ ላደረጉት አስተዋፅኦ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ሊቀመንበሯ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ተግዳሮትም እንዲህ ሲሉ አስቀምጠዋል፡- “እንደ ኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርነትዎ በአገር ውስጥ በርካታ ተግዳሮቶችን እየተጋፈጡ ነው፤ የክልል እና የብሔር ክፍፍል ወደ 3 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል። እነዚህ ሰዎች በራሳቸው አገር ቤት አልባ ሆነዋል። እነዚህ ሰዎች ወደ ቀያቸው መመለስ አለባቸው። የኢኮኖሚ ቀውስ፣ ሥራ አጥነት፣ ትምህርት እና ጤና ላይም መሠራት አለባቸው”
በሽልማቱ ወቅት በኖርዌይ “የኢትዮጵያና የኤርትራ ሰላም በሚገባ አልተረጋገጠም፤ የኖቤል ሽልማት ሊሰጣቸው አይገባም” በሚል ካደረጉት የተቃውሞ ሰልፍ ጀምሮ በአገር ውስጥም በውጪም ያሉ ኢትዮጵያውያንም ሽልማቱን ሲቃወሙ ታይተዋል። ከመቃውምም አልፈው ራሴን ጨምሮ ደስ ብሎናል ያሉትን “አይ አበሻ” ሲሉ አንጓጠዋል። በቀልድም በቧልትም በኩል በቀንደኛ ደጋፊነት የማይታሙ የመጀመሪያ ሰሞን አድናቂዎች ፣ነገር ግን በሽልማቱ ደስታቸውን የገለፁትን “ዳግም ተደማሪ” እስከማለት ደርሰዋል።
በበኩሌ የግሌን አቋም ያስረዳልኛል ያልኩት አቋም ቴዎድሮስ ተክለአረጋይ የተባሉ ጋዜጠኛ በማኅበራዊ ገጻቸው ያሰፈሩት ነው። “የ2019 የዓለም የሰላም ሽልማት ከመላው ዓለም መሪና አገር ለእኛው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድና ለኢትዮጵያ ነው የተሰጠው። ለሌላ ለማንም አልተሰጠም። ለማንም። በዚህ አለመደሰት ማንስ ጤነኛ አዕምሮ እንዴት ይችላል? ጠቅላይ ሚኒስትሩን መደገፍ ሲያስፈልገኝ እደግፋቸዋለሁ። ቅሬታም ሲኖረኝ እቃወማቸዋለሁ። ኢትዮጵያን ማሸለማቸው ላይ ግን አንዳችም ተቃውሞ ሊኖረኝ አይችልም። ምንም ምክንያት ሳልፈልግ እደግፋቸዋለሁ። እናም ደግሞ አገሬን በኖቤል መዝገብ ላይ በማስመዝገባቸው አመሰግናቸዋለሁ።”
እንጂማ የምናዝንበት፣ ገና ብዙ ይቀረናል የምንልበት ብዙ የቤት ሥራ አለን። ትናንት እሳቸው በኖርዌይ ሽልማታቸውን ሲቀበሉ እንኳን እዚህ አዲስ አበባ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ዩ ኤን ዲ ፒ በድህነት መለኪያ አሁንም ከዓለም ጭራ ላይ መሆናችንን የሚገልጽ ሪፖርት አውጥቶ ነበር። በየዓመቱ በሚያውጣው በዚህ ሪፖርት የዚህ ዓመት ትንተና መሠረት ከኢትዮጵያ አጠቃላይ ሕዝብ 83 በመቶ የሚሆነው በዘርፈ ብዙ ድህነት (Multidimensional poverty) ውስጥ ይኖራል። ዘርፈ ብዙ ድህነት በጣም ዝቅተኛ የሆነ የአኗኗር ሁኔታ፣ የጤናና የትምህርት እጦትን በመሠረታዊነት የሚያካትት መለኪያ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በዚህ ዘርፍ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገራት ካሳዩት አማካይ ቁጥር ዝቅ ያለ ደረጃ ኖሯት ዩጋንዳና ሩዋንዳ ያሉት አገራት የተሻለ ደረጃ ላይ እንዳላቸው ተመልክቷል።
በሪፖርቱ እንደተቀመጠው በገጠር በድህነት ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውን በትምህርት፣ ንጹህ የመጠጥ ውሃ፣ ንጽህና አገልግሎት፣ ኤሌክትሪክና ቤት የመሳሰሉት አገልግሎቶች እጦት አለባቸው። ከዚህ ጋር ተያይዞ በውሃ ወለድና ከንጽህና ጉድለት በሚመጡ በሽታዎች በተለይ ህፃናት በለጋ እድሜያቸው እንደሚቀጠፉም የሚታወቅ እውነት ነው።
ወደ መፍትሔው ስንመጣ በተለይ ይህ እንዲህ ሆነ ያ እንዲህ ሆነ እያልን አስተያየት መስጠት የሚቀናን ዜጎች፣ ሁሉን ለመንግሥት መተውን አቁመን የድርሻችንን ልንወጣ የግድ ይላል። መንግሥት እየጀመራቸው ላለው ማኅበራዊ ግልጋሎቶችና የበጎ ፈቃድ ሥራዎች አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ፣ መንግሥታዊ ያልሆኑና አገር በቀል ተቋማት ዜጎችን ለመርዳት የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች በግልም ይሁን በመሥሪያ ቤቶቻችን አካባቢዎች በመሰባሰብ ድጋፍ ማድረግ ምናልባት ከራስ ህሊና ወቀሳ ለመዳን የመጀመሪያ እርምጃ ሊሆን ይችላል።
‹አገሬ ምን አደረገችልኝ ሳይሆን፣ ለአገሬ ምን አደረኩላት በሉ› እንደተባለውም እንደ ዜጋ ከእያንዳንዳችን የሚጠበቅ መኖሩን አለመዘንጋት፣ ቢያንስ ለልጆቻችንና ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች አገር ለማውረስ፣ ለራሳችን የተሻለ ነገ ብንሠራስ?
ቤተልሔም ነጋሽ የፖለቲካ ተግባቦት ባለሙያ ናቸው።
በኢሜይል አድራሻቸው
[email protected] ይገኛሉ።
ቅጽ 2 ቁጥር 58 ታኅሣሥ 4 2012



