በአሶሳ ከተማ የፍራፍሬ ማቀነባበሪያዎች ፋብሪካ ሊገነቡ ነው

0
728

የአሶሳ ገበሬዎች ኅብረት ሥራ ማኅበር ከፌዴራል ኅብረት ሥራ ማኅበር ጋር በመቀናጀት የማንጎ እና የቲማቲም ምርቶችን በማቀነባበር ለገበያ የሚያቀርብ ፋብሪካ ከ179 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ሊገነቡ እንደሆነ አስታወቁ።
ለአንድ መቶ ሰዎች የሥራ እድል ይፈጥራል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ፣ በአሶሳ ከተማ በኅብረት ሥራ ማኅበሩ ግቢ ውስጥ የሚገነባ ሲሆንኅ በዓመት 180 ሺሕ ቶን የማንጎ ፍሬን እና 108 ቶን ቲማቲምን በማቀነባበር በዓመት 954 ሺሕ ቶን ማርማራታ፣ 13 ሺሕ ቶን በላይ የማንጎ ጭማቂ እና ከ 1ሺሕ 900 ቶን በላይ የቲማቲም ድልህ የማምረት አቅም ይኖረዋል ተብሏል።
የሚገነባው ማቀነባበሪያ ፋብሪካም የፍራፍሬ ምርቶች ከተመረቱ በኋላ የሚደርሰውን ብክነት ለመቀነስ ይረዳል የተባለ ሲሆን፣ ወቅትን ተከትሎ በፍራፍሬ ገበያው ላይ የሚታየውን ችግር ከመቅረፍም በላይ ገበሬዎች ባመረቱት ምርት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንደሚያስችላቸው ተገልጿል። በዓመትም ከ 400 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን ማንጎ እና የቲማቲም ምርቶችን እንደሚገዛ ተገልጿል።
የኅብረተሰቡ የኑሮ ዘይቤ መለወጡን ተከትሎ እየጨመረ የመጣውን የታሸጉ ምርቶች ፍላጎት ለገበያ መዳረሻነት መሠረት ያደርጋል የተባለ ሲሆን፣ ከውጪ የሚገቡ የቲማቲም ድልህ፣ ጭማቂዎችን በአገር ውስጥ ምርቶች ለመተካት እና ወደ ውጪም ለመላክ ያስችላል ተብሏል።
በዓመትም በኢትዮጵያ የማርማራታ ፍላጎት 12 በመቶ፣ የማንጎ ጭማቂ ፍላጎት 22 በመቶ እንዲሁም የቲማቲም ድልህ ፍላጉት 5 በመቶ በማደግ ላይ ይገኛል።
በአካባቢው እነዚህ ፍራፍሬዎች በስፋት በሚደርሱባቸው ወራት ሳይበላሹ ለማቆየት አለመቻሉን ተከትሎ፣ ምርቶቹን ለማምረት ከወጣባቸው ወጪ ባነሰ በቅናሽ ለገበያ ይቀርባሉ። የፋብሪካው መከፈት ምርቶቹ በማይኖሩባቸውም ወቅቶች ጭምር ለመጠቀም የሚያስችል እና አምራቾች ፍራፍሬዎችን በተሻለ መጠን እንዲያመርቱ ለማድረግ እንደሚረዳ ተገልጿል።
በኢትዮጵያ ማንጎ በቤኔሻንጉል፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይ እና በደቡብ ክልሎች የሚመረት ሲሆን፣ ከሙዝ እና ከአቮካዶ በመቀጠል ከፍተኛ የምርት መጠንም ይዞ በዓመት እሰከ 100 አምስት ሺሕ ሜትሪክ ቶን በላይ በመመረት ላይ ይገኛል። በአንፃሩ ቲማቲም ከባህር ጠለል በላይ ከ700 እስከ 2000 ሜትር ከፍታ ባላቸው ቦታዎች ላይ ዓመቱን ሙሉ የሚበቅል ምርት ነው።
ደቡብ ክልል ከ3 ሺሕ ሄክታር በላይ የማንጎ እርሻን በመያዝ ቀዳሚ ስፍራ ላይ ይገኛል። በኹለተኛ ደረጃ ላይም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኝ ሲሆን፣ 652 ሺሕ ሄክታር መሬት በማንጎ ዛፍ የተሸፈነ ነው። እንደ ማዕከላዊ ስታስቲክስ መረጃ ከሆነ፣ የጋምቤላ ክልል የማንጎ ሰብል 180 ሄክታር አካባቢ የሚሸፍን ሲሆን የትግራይ ክልል 118 ሺሕ ሄክታር የማንጎ ምርት አለው።
በ36 ሺሕ ሄክታር ላይ በስፋት የሚለማው እና በአገሪቱ ከፍተኛ ምርት በመስጠት ተወዳዳሪ የሌለው ፍራፍሬ ዝርያ፣ ሙዝ፣ በዓመት ከ3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይሰጣል። አቮካዶ 9 ሺሕ ሄክታር መሬት ላይ በመልማት በየ ዓመቱ 256 ሺሕ በላይ ኩንታል ምርት ይሰጣል።

ቅጽ 2 ቁጥር 58 ታኅሣሥ 4 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here