ጀግኒት! አረአያም! አሸናፊም!

0
780

በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሴቶች ከሚያጋጥሟቸው ማኅበረ ፖለቲካዊ ተግዳሮቶች በተጨማሪ ተፈጥሮ በራሱ አንዱ ፈተና ሆኖ ቆይቷል። ብዙ ሴቶች የወር አበባ አጸያፊና ነውር ነው ተብለው ስላደጉ ስለጉዳዩ ለመወያየትም ሆነ በምን መልኩ ንጽህናቸውንና ጤናቸው መጠበቅ እንዳለባቸው በቂ ግንዛቤ የላቸውም። ምንም እንኳን ጉዳዩ በገጠሪቱ የአገራችን ክፍል የከፋ ቢሆንም፣ ከተማ ተወልደው ያደጉ ሴቶችም ከችግሩ የድርሻቸውን ይወስዳሉ።
ሌላው ቢቀር እንኳን ሱቅ ሔደው ሞዴስ ለመግዛት መሸማቀቃቸው አይቀርም። ባለ ሱቁም ቢሆን የገዙትን ሞዴስ ሲሰጣቸው እንዳይታይ በጥቁር ፌስታል ወይንም በወረቀት ጠቅልሎ ነው። ግና ይህንን ሞዴስ የመግዛት እድል የሚያገኙት ጥቂት ሴቶች ብቻ ሲሆኑ፣ ብዙኀኑ ሴቶች የወር አበባቸው ሲመጣ በጭንቀት፣ የወር አበባቸው የመጣበትን ቀን በመርገምና ከትምህርት ገበታቸው በመቅረት ነው የሚያሳልፉት።
ለዚህም ዋናው ምክንያት የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ እንደ ቅንጦት ዕቃ ተቆጥሮ ከፍተኛ ቀረጥ የተጣለበት መሆኑ ነው። ይህንን ችግር ለመቅረፍ በተለያዩ ተቋሞችና ግለሰቦች በርካታ እንቅስቃሴዎች የተደረጉ ቢሆንም፣ ችግሩን ለመቅረፍ ከመንግሥት ቀድመው መፍትሔ ለመስጠት ቁርጠኝነት ካሳዩ ሰዎች መካከል ፍሬወይኒ መብርሀቱ በቀዳሚነት የምትጠቀስ ናት።
ፍሬወይኒ በኬሚካል ኢንጂነሪንግ ዲግሪዋን በአሜሪካን አገር ከሚገኝ ዩኒቨርሲቲ አግኝታለች። በኋላ በአውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር 2005 ላይ ወደ አገሯ በመመለስ፣ ታጥቦ በድጋሚ አገልግሎት ላይ ሊውል የሚችል የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ሞዴስን ዲዛይን በማድረግ ፋብሪካዋን አቋቁማለች። በዚህ ታጥቦ በድጋሚ እስከ አንድ ዓመት ድረስ አገልግሎት ላይ ሊውል በሚችለው የንጽህና መጠበቂያ ሞዴስ፣ ወደ 800 ሺሕ የሚጠጉ ሴቶች ተጠቃሚ የሆኑ ሲሆን ፍሬወይኒ በድርጅቷ አማካኝነት እስከ 750 ሺሕ የሚደርሱ ሞዴሶችን በዓመት ውስጥ የማምረት አቅም አላት።
ፍሬወይኒ ሰማንያ በመቶ የሚሆነውን ምርቷን ከእርሷ ገዝተው የገንዘብ አቅማቸው ደከም ላለና ገዝቶ ለመጠቀም አቅም ለሌላቸው ሴቶች ለሚያሰራጩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ነው የምትሸጠው። ታጥበው በድጋሚ ጥቅም ላይ የሚውሉ የንጽህና መጠበቂያ ሞዴሶችን ከማቅረብ ባሻገር፣ የወር አበባን እንደ ነውር የሚቆጥረውን ባህላችንን ለማስቀረት በትምህርት ቤቶች ውስጥ ንግግር በማድረግ እንዲሁም ሴትና ወንድ ልጆችን በማስተማር የበኩሏን አስተዋጽኦ ለአስራ አራት ዓመታት ስታበረክትም ቆታለች።
ይህ ጥረቷም የበርካታ ሴቶችን ሕይወት ከመቀየር ባሻገር ዓለም ዐቀፍ እውቅና አትርፎላታል። በመሆኑም የ2019 የሲ ኤን ኤን ጀግኒት በመሆን አሸንፋለች።
መንግሥትም ቢሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያን ከቅንጦት ዕቃ ዝርዝር ውስጥ በማውጣት በመድኀኒት ጤና አገልግሎት ዘርፍ እንዲካተት የጤና ሚኒስቴር ወስኗል። ይህንኑ ተከትሎም የሞዴስ ዋጋ በግማሽ እንደሚቀንስ ይጠበቃል። ይህ መልካም ዜና ሆኖ ሳለ የፖሊሲ ውሳኔው እስከ አሁን ለጉምሩክ ኮሚሽን እንዳልደረሰ የኮሚሽኑ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ወንድወሰን ደገፋ ባሳለፍነው ሳምንት ለአዲስ ማለዳ መግለጻቸው አሳሳቢ ነው።
በመሆኑም መንግሥት ለጉዳዩ አፋጣኝ ምላሽ እንደሚያስፈልገው ተረድቶ ፖሊሲውን በአፋጣኝ ለጉምሩክ ኮሚሽን በመላክ ሕጉ በተግባርና በቶሎ እንዲፈጸም እጠይቃለሁ/ እንጠይቃለን። ከመንግሥት በተጨማሪም ፍሬወይኒን በአረአያነት በመውሰድ ስለ ጉዳዩ ያገባኛል የምንል ግለሰቦች ሁሉ መፍትሔ ይሆናል የምንለውን ሐሳብ ወደ መሬት በማውረድ የእህቶችን ፈገግታ እንመልስ ዘንድ ጥሪዬን አቀርባለው።
ኪያ አሊ

ቅጽ 2 ቁጥር 58 ታኅሣሥ 4 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here