የአዋሽ-ወልዲያ-ሃራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት የኤሌክትሪክ ሃይል እንዲቀርብለት ተወሰነ

0
2217

ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ የኤሌክትሪክ ኃይል ባለማግኘቱ ምክንያት ወደ ሥራ መግባት ያልቻለው የአዋሽ-ወልዲያ-ሃራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት፣ ኃይል እንዲቀርብለት ማክሰኞ ኅዳር 30/2012 በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት በተደረገ እና ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተሳተፉበት ስብሰባ ተወሰነ።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የመሠረተ ልማት አማካሪ ዣንጥራር አባይ የመሩት እና የትራንስፖርት ሚኒሰቴር፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኀይል፣ የገንዘብ ሚኒስቴር እንዲሁም የባቡር ኮርፖሬሽን የተሳተፉበት ይህ ስብሰባ፣ ሲያወዛግብ የቆየውን የገንዘብ ምንጭ የባቡር ኮርፖሬሽን እንዲሸፍን ስምምነት ላይ ተደርሷል።
‹‹እስከ አሁንም ምንም አይነት ውዝግብ አልነበረም፣ ለዚህ ሥራ የተያዘ በጀት ስላልነበረ ክፍተቱ ተፈጥሯል፣ አሁን ግን ወጪው በኮርፖሬሽኑ ተሸፍኖ ኃይል እንዲቀርብ ተወስኗል›› ሲሉ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለደ ተናግረዋል።
በዚህም መሠረት ጨረታ ወጥቶ ኃይል ወደ ባቡር ፕሮጀክቱ የሚወስደው መሠረተ ልማት ግንባታ ሥራ በቅርቡ ይጀመራል ያሉት አብርሃም፣ ሥራው ተጠናቆ ኃይል ወደ ባቡር ፕሮጀክቱ እስኪደርስ ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ ጊዜ እንደሚወስድ ተናግረዋል።
የግንባታው አጠቃላይ ወጪም የፕሮጀክቱን ኹለት በመቶ የሚያክል ሲሆን፣ በዚህ መሰረትም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ የሥራ እቅድ በማውጣት እንደሚያስታውቅ ይጠበቃል።
በቱርኩ ግዙፍ ኩባንያ ያፒ መርከንዚ የተገነባው የአዋሽ-ወልዲያ-ሃራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት የመጀመሪያ ክፍል አንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ዶላር የጠየቀ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥም 300 ሚሊዮን ዶላሩን የቱርክ ኢምፖርት ኤክስፖርት ባንክ ሸፍኗል። ይህም በወቅቱ ቱርክ ለውጪ አገራት ከሰጠቻቸው ብድሮች ትልቁ ነበር። ቀሪውን አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላር ፋይናንስም ከአውሮፓ የገንዘብ ምንጮች የተገኘ ነበር።
የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የባቡር መስመር ግንባታው ቢጠናቀቅም ለወራት የኤሌክትሪክ ኃይል ባለመቅረቡ ከፍተኛ የአገር ሃብት የፈሰሰባቸው ንብረቶች ለብልሽት እና ለስርቆት መዳረጋቸውን ሲያሳስብ ቆይቷል። ከዚህ በተጨማሪም የግንባታ ሥራው በመጠናቀቅ ላይ ቢሆንም የኃይል አቅርቦት ባለመኖሩ ሙከራ ለማድረግ እንኳን አለመቻሉ በኮርፖሬሽኑ በኩል በተደጋጋሚ ይፋ ሲያደርግ ቆይቷል።
የኤሌክትሪክ ኃይልም የባቡር መስመር ግንባታውን መገባደድ አስመልክቶ የመስመር ዝርጋታውን እንዲፈፅም በተደጋጋሚ መጠየቁን፣ ሆኖም ግንባታው 40 በመቶ ከደረሰበት ጊዜ ጀምሮ ከኮርፖሬሽኑ ጋር በአካል በመገናኘት እንዲሁም ደብዳቤዎችን በመለዋወጥ የገንዘብ ምንጭ እንዲፈልጉ አሳስበናል የሚሉ ምክንያቶችን ሲያነሳ መቆየቱን አዲስ ማለዳ መዘገቧ ይታወሳል።
የኤሌክትሪክ ኃይል የመሰረተ ልማት ግንባታውን ለማከናወን ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ እንዲሁም ረዥም ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ፣ በግንባታው እና በኀይል አቅርቦቱ መካከል ለሚፈጠረው አለመጣጣምም ኀላፊነቱን እንደማይወስድ በተጨማሪም ወጪውን የሚሸፍንበት ምክንያት እንደሌለ በማንሳት ኮርፖሬሽኑ የገንዘብ ምንጭ አፈላልጎ እንዲያመጣ ሲያሳስቡ መቆየታቸው ይታወሳል።
በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘው የአዋሽ- ኮምቦልቻ -ሃራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት 392 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ሲሆን፤ ዋና ጣቢያውን ኮምቦልቻ በማድረግ በ20 የእቃና 6 የሰው ማጓጓዣ ባለተጎታች ባቡሮች አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል። ከ3 ሺሕ 500 በላይ ኢትዮጵያውያን ሠራተኞች በተለያዩ የሙያ ዘርፎች የሥራ ዕድል ፈጥሮ የነበረው ፕሮጀክቱ፣ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ስለ ባቡር ቴክኖሎጂ ሥራዎች ግንዛቤ እና ችሎታ እንዲኖራቸው ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ነበረው።

ቅጽ 2 ቁጥር 58 ታኅሣሥ 4 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here