አስተማሪው ሕዝብ ነው!

0
665

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሥልጣን ላይ ከወጡበት የመጀመሪያው ሦስትና አራት ወራት ውጪ የሕዝብ ድጋፍ አንዳንዴ የሚጨምር አንዳንዴ የሚቀንስ ሆኖ ታይቷል። የመጀመሪያዎቹ ጥቂት የድጋፍ ወራት ከዴሞክራሲያዊ የፓርቲ ምርጫ፣ መፈንቅለ መንግሥት እና አብዮት ድቅል ለሚመስለው ለውጥ እና አብዮት ላስመሰለው ረጅም ጊዜ የወሰደ የሕዝብ ትግል የጫጉላ ጊዜ ነበር። የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራኑ እንደሚሉት መዋለል (Oscillation) ከሚባለው የአብዮት ደረጃ ጋር በተመሳሳይ ሁኔታ ላይ ይገኝ የነበረው አዲሱ መንግሥት፣ ድሉን ከሕዝብ ጋር በሰፊው አክብሮ ነበር። ጊዜውን በትክክል በሚገልጽ ሁኔታም የለውጡ ግንባር ቀደም ተዋንያን በተደጋጋሚ “ለውጡን የማይቀለበስበት ደረጃ” ስለማድረስ ያወሩ ነበር።
በዚህ ከፍተኛ የሕዝብ አንድነትና የመንግሥት ሕዝባዊነት ወቅት ሕዝቡ ለረጅም ጊዜ ሰምቶት በማያውቀው ደረጃ የአንድነትና የኢትዮጵያዊነት ስሜት በለውጥ ኃይሉ ይሰበክ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በተለያዩ ከተሞች እየተንቀሳቀሱ ያደረጓቸው ንግግሮች፣ በአውሮፓና በአሜሪካ የለውጥ ኃይሉ መሪዎች ያደረጓቸው ከፍተኛ ድጋፍ የነበራቸው ጉብኝቶችና ውይይቶች እንዲሁም የመስቀል አደባባዩ የድጋፍ ሰልፍ የሕዝብን አንድነት መፈለግ የሚያሳዩ እና የለውጡም ኃይል ይህን ሊያሳካ የሚችል መሆኑን ተስፋ ያጫሩ ነበሩ።
በተለይ በመስቀል አደባባዩ የድጋፍ ሰልፍ ጊዜ እንደታየው በሕዝቡ የተፈጠረው ጥሩ ስሜት፣ ለውጡ ምንም ዓይነት አደጋ እንዳያጋጥመው ዘብ ለመቆም ዝግጁ ነበር።
ሕዝብ ይህን ሁሉ ድጋፍ ሲሰጥ፣ ሥልጣን ላይ የወጡት ሰዎች በኢሕአዴግ አባልነታቸው ድርጅቱ ሲፈፅም ለኖረው የመብት ጥሰት፣ ግድያ እና ዝርፊያ የበኩላቸውን ያበረከቱ መሆናቸውን ዘንግቶት አይደለም። ይልቁንም በሕወሃት ይመራ የነበረውን የኢሕአዴግ መንግሥት ለሕይወታቸው ሳይሳሱ ታግለው ከውስጡ ለሕዝብ ተስፋ የሚሰንቅ ኃይል መሆናቸው ሀጢያታቸውን ማስተሰሪያ ንስሃቸው ነው ብሎ በማመኑ ነው። በመሆኑም ይቅርታ የሚያባብል ነገር በሌለበት መልኩ ሙሉ ድጋፉን በመስጠት የኋላውን ትቶ የአሁኑንና የነገን ብርሃን እያሰበ ከጎናቸው ለመቆም ጊዜ አልፈጀበትም።
በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር የለውጡ መሪዎች ያካሔዷቸው ስብሰባዎች ላይ ሕዝቡ ያሳያቸው ፍቅር ለዚህ ማረጋገጫ ነው። ከዚያም አልፎ የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት ተጭኖት የነበረው ትቢያ መገፈፉን የኹለቱ አገራት መሪዎች ሲያበስሩ፣ ሕዝቡ ተለያይቶ የቆየበት ኻያ ዓመታት እንዳላረሳሳው አሳይቷል።
በዚህ ጊዜ መሪዎቹ መጀመሪያ ሒሳባችንን አወራርደን ሰላምን ኹለተኛ እናደርጋለን ያለማለታቸው የስኬታቸው ቁልፍ ነው። ከዚያ ይልቅ የሚቀድመው ሰላም መኖሩ ነው፤ ያሉትን ችግሮች በመተሳሰብ ለወደፊት እንፈታቸዋለን ማለታቸው በዚህ ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኖቤል የሰላም ሽልማትን እንዲቀበሉ አድርጓቸዋል። ይህ ሆደ ሰፊነትና አርቆ አሳቢነት በዚህ የብልጣ ብልጥነትና የጉልበት ዘመን እውነትም ሊያሸልም ይገባል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተነሳሽነቱን በመውሰድ ለእርቅና ይቅር ለመባባል ምክንያት መሆናቸው የተለመደ የፖለቲከኛ ባህሪይ ያለመሆኑን ዓለም ጭምር በማረጋገጥ ይህንን ሽልማት አበርክቶላቸዋል። በተቃራኒው ግን ይቅር መባባል የሕዝብ ባህርይ ነው። እንጂ የፖለቲከኞች አይደለም በመሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኖቤል ሽልማቱን ያሸነፉት ከመደበኛው የፖለቲከኛ አካሔድ ይልቅ የሕዝብን ዓይነት ባህሪይ ስላሳዩ ነው።
ቀደም ብሎ እንደተጠቀሰው ሕዝቡ የአዲሱ መንግሥት ባለሥልጣናት በኢሕአዴግ ውስጥ ላደረጉት ሁሉ ይጠየቁ አላለም። ከአራት እና አምስት ወራት በኋላ መንግሥት አካሔዱን ሲቀይርና ፖለቲከኞቹ እንደልማዳቸው በየብሔራቸው ጎራ ገብተው ሲሻኮቱም፣ ሰፊው ሕዝብ በትዝብት ተመልካች ነበር። ቁጥራቸው ጥቂት የሆኑ የሕዝብ ክፍሎች ግን የፖለቲከኞች መሣሪያ በመሆን የተቀረውን ሕዝብ ሲያንገላቱ፣ ሲያፈናቅሉ እና ሲገድሉ አይተናል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን ላይ ከነበሩበት ጊዜ ውስጥ ከአንድ ዓመት በላይ የብሔር ተኮር ጥቃቶች፣ የመንግሥት ዳር ቆሞ ተመልካችነት፣ የፍትኅ መጓደል፣ ወገንተኝነት እንዲሁም አጠቃላይ የሰላምና ደኅንነት እጦት የታየበት ነበር። በዚህም ብሔር በማይገድበው መልኩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የሚነሱ ቅሬታዎች ነበሩ።
በዚህ ሳምንት በኖርዌይ ዋና ከተማ ኦስሎ በተካሔደው የዓለምን ቀልብ የሳበ የኖቤል የሰላም ሽልማት ጊዜ እንደታየው ግን፣ በውጪም ሆነ አገር ውስጥ ያለው ሕዝብ እጅጉን ተደስቷል። ይህም የሆነው አገር በጥሩ ነገር ስለተነሳች ነው። ካሳለፍነው የመከፋፈልና የመናቆር ጊዜያት አንጻር ቢሆን ኖሮ በኖርዌይ ያሉ ኢትዮጵያውያን የመሪያቸውን እጅ ለመጨበጥና አንገታቸውን ለማቀፍ ባልተሯሯጡ ነበር። ወደ አገራቸው ሲመለሱም ማንም ጠራ ማንም፣ ሕዝቡ ቤቱ ክትት ብሎ ባሳለፈ ነበር።
ነገር ግን የሆነው ተቃራኒው ነው። አሁንም በድጋሚ ሕዝብ የሚያስጨንቀው የአገር ጉዳይ እንጂ የፖለቲከኞች ጨዋታ እንዳልሆነ አሳይቷል። ምንም እንኳን በፖለቲከኞች የሚሠሩ ጥፋቶች የሚያቃቅሩ እና የሚከፋፍሉ ቢሆኑም፣ ሕዝብ ግን ወደ ኅብረት ለመመለስ አንድ አጋጣሚ ብቻ እንደሚጠብቅ አሳይቷል።
በመሆኑም በተደጋጋሚ ለሥልጣን ሩጫቸው፣ ለጥቅማቸው ወይም ለተወሰነ ቡድን ላላቸው ጥላቻ ማራገቢያ ሲሉ የሕዝብን የጋራ ባህሪይ አጥፍተው ወደ ጥፋት የሚመሩ የአገራችን ፖለቲከኞች የሕዝባቸውን ፍላጎት ለማጤን፣ የዚህ ሳምንቱ ድጋፍ ሁነኛ አጋጣሚ ነው። ፖለቲከኞቻችን በተደጋጋሚ እንደታየው ረጅም ጊዜ የቆጠረውን የሴራ ፖለቲካ መሻገር አሁንም እንዳዳገታቸው ነው።
ነገር ግን ይህ የሴራ ጉንጉን ከእነሱ አልፎ ሕዝብን እንዲያቃቅር፣ እንዲከፋፍል እንዲሁም እንዲያጋድል ሊፈቀድለት አይገባም። በተደጋጋሚ በፖለቲከኞች መካከል ያሉ የኃይል አሰላለፎች መቀያየር ሕዝብን ሲከፋፍሉ አይተናል። ነገር ግን ፖለቲከኞች ቋሚ ወዳጅና ጠላት የሌላቸው መሆኑ ታውቆ፣ ጉዳዩ ወደ ሕዝብ እንዳይወርድ ማድረግ ይገባል ስትል አዲስ ማለዳ ታምናለች።
በየጊዜው የመለያያ ነጥቦችን እያነሱ እና የጋራ የሆኑትን ጉዳዮችም ጭምር ከአንድ ቡድን አንፃር ብቻ እየቃኙ ያለመግባባትን እና ቁርሾን በሕዝብ መካከል መፍጠር መቆም አለበት። ይልቁንም ፖለቲከኞቻችን በተለምዶ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ሲያደርጓቸው የቆዩትን ነገሮች ሳይሆን ሕዝቡ በብሔር፣ በሐይማኖት ራሱን ሳይከፋፍል በኅብረት የሚደምቅባቸውን ጉዳዮች በማየት አጀንዳቸውን ሕዝቡን በዚህ መንገድ ሊያሰልፍ በሚችል ሁኔታ ሊያራምዱ እንደሚገባ አዲስ ማለዳ አጽንኦት ትሰጣለች። በዚህ ዓይነት መንገድ ተቀባይነታቸውን ሊጨምሩ የሚችሉ ሲሆን ለሕዝብም ተስፋና ሰላምን ሊሰጡ ይችላሉና።

ቅጽ 2 ቁጥር 58 ታኅሣሥ 4 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here