ሐሙስ ሐምሌ 04 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል በቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ውስጥ የሚገኝ በሕጋዊ መንገድ ለቤተ ክርስቲያኗ ከተላለፈ የመሬት ይዞታ ላይ 40 ሺህ ካሬ ሜትር የሚሆነውን በግድ ተነጥቀናል ሲል አስታወቀ።
ይዞታውን በሀይል በመቀማት ለሁለት ግለሰቦች እንደተሰጠ የተገለጸ ሲሆን ጉዳዩን አስመልክቶ ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ ይዞታው የቤተ ክርስቲያኗ እንደሆነ ተወስኖ ነበር።
ይሁን እንጂ የከተማ አስተዳደሩ ግንባታውን እያጓተተ እና እያዘገየ ስለነበር ለኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እና ለፌደራል መንግስት ቅሬታ አቅርበው በከፍተኛ አመራር ደረጃ ኮሚቴ ተዋቅሮ እየታየ ባለበት ሁኔታ በትናንትናው ዕለት በሐምሌ 03 ቀን 2016 የከተማ አስተዳደሩ ባለሙያዎችን እና ወታደሮችን ይዞ በመግባት ችካል በማስቀመጥ የቤተ ክርስቲያኗን ንብረት ለግለሰብ መስጠቱን ካውንስሉ ለአዲስ ማለዳ በላከው መግለጫ ገልጸዋል።
ይህ ሕገ ወጥ ድርጊት መንግስትን የማይወክል የጥላቻ ተግባር መሆኑን ያመላከተው መግለጫው በልማት ሰበብ ከመንግስት ጋር ለማጣላት ሆን ተብሎ እየተሰራ ያለ ነው ብሏል።
በልማት ሰበብ የሚደረገውን ሕገ መንግስትን የጣሰ ተግባር፤ የሚመለከታቸው አካላት፣ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እና የፌደራል መንግስት ከፍተኛ አመራሮች ሕግን እንዲያስከብሩም የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተክርስቲያናት ካውንስል አሳስቧል።



