ያለ አግባብ ከስራ ገበታችን እንድንባረር ሆነናል ያሉ 92 የሞሃ ለስላሳ ድርጅት ሰራተኞች ቅሬታቸውን አሰሙ

0
855

በአለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆኑ የፔፕሲና የሚሪንዳ ምርቶችን በብቸኝነት ለሀገር ውስጥ ገበያ በማቅረብ የሚታወቀው ሞሐ የለስላሳ መጠጦች ኢንዱስትሪ ያለ አግባብ የስራ ውላችን እንዲቋረጥ አድርጓል ሲሉ የድርጅቱ ሰራተኞች ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡

ንብረትነቱ የኢትዮጵያዊው ባለሃብት ሼክ መሐመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲ የሆነው እና በቅርቡ በሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ስር እንዲቀላቀል የተደረገው ሞሐ ያለአግባብ ከስራ ገበታችን እንድንቀነስ ሆነናል የሚሉት ሰራተኞቹ ይህም ከአዲሱ አድሎአዊ የድርጅቱ አወቃቀር ጋር የሚያያዝ ነው ይላሉ፡፡

ድርጅቱ ከፍተኛ የገበያ ድርሻ በመያዝ ይሰራል ተብሎ ቢታሰብም በነበረው የአመራር ችግር ለዓመታት በኪሰራ ውስጥ ማሳለፉን ተከትሎም የማገገሚያ እርምጃዎችን እየወሰደ ስለመሆኑ በአንድ ወቅት አሳውቆ እንደነበር አይዘነጋም፡፡

ከነዚህ ድርጅታዊ የማገገሚያ እርምጃዎች ውስጥ የሰው ሃይሉን እንደ አዲስ ማዋቀር አንዱ ሲሆን ይህ እየተደረገ ያለው አዲስ ድልደላም ሆነ የስራ ውል ማቋረጫ ሂደቱ ተገቢውን ህጋዊ መስመር አለመከተሉ ዋነኛ ቅሬታቸው መሆኑን የሚገልጹት የድርጅቱ ሰራተኞች ሰራተኛው ያላመነበትንና ያልተወያየበትን መመሪያ አዘጋጅቶ በማጽደቅ እና ኮሚቴ በማዋቀር ከየካቲት 14 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ሰራተኞችን ማሰናበት መጀመሩን ያነሳሉ፡፡

ከተለያዩ የድርጅቱ ቅርንጫፎች የድልደላ ቅነሳ መደረጉን የጠቆሙት ቅሬታ አቅራቢ ሰራተኞች ለእያንዳንዱ ሰራተኛ ከሚያዝያ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ የሁለት ወር የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ከሰኔ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ከፋብሪካው ጋር የነበራቸውን ውል እንዲቋረጥ ማድረጉን ከደረሳቸው ደብዳቤ ጋር አያይዘው ጠቁመዋል፡፡

ከድርጅቱ ቅርንጫፎች መካከል በአዲስ አበባ ሰሚት ከሚገኘው ድርጅት 187 ያህል ሰራተኞች ከስራገበታቸው የተነሱ ቢሆንም 95ቱ ወደ ስራ ገበታቸው መመለሳቸውን ጠቁመው 92 የሚሆኑት ሰራተኞች ግን እስካሁን ወደ ስራ እንዳልተመለሱ እና ችግር ላይ መሆናቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ በግንቦት 29 ቀን 2016 ዓ.ም በተክላይሃይማኖት ፋብሪካ የሚገኙ ሰራተኞችን የስራ ዉል መቋረጡን የሚገልጽ ደብዳቤ መፃፉን ተከትሎ ከስራ ገበታቸው ያለ አግባብ እንዲቀነሱ መደረጋቸውን አዲስ ማለዳ ከምንጮቿ አረጋግጣለች፡፡

ሰራተኞቹም በቀድሞ አመራሮች ምክንያት ድርጅቱ ለኪሳራ የተዳረገ ቢሆንም ሰራተኞቹን ያለበቂ ምክንያት ከስራ ማሰናበት ተቀባይነት የሌለዉ ነዉ ብለዋል።

አክለውም እረጅም አመት የሰሩ እና አቅመ ደካማ የሆኑ ችግር ላይ መውደቃቸውን እንዲሁም የተሰጣቸው ካሳም በቂ አለመሆኑን በማንሳትም አፋጣኝ ምላሽ እንፈልጋለን ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

20 እና 19 አመት ሲሰሩ የቆዩ ሰራተኞች ወደ 60ሺ ብር አካባቢ የካሳ ክፍያ ብቻ እየተሰጣቸው እንዲሰናበቱ መደረጉም አግባብነት የሌለው አሰራር ስለመሆኑ ነው ያነሱት፡፡

በሰሚት ቅርንጫፍ ይሰሩ የነበሩ የቀድሞ የሞሃ ሰራተኞች ቅሬታችንን ሰምቶ መፍትሄ የሚሰጠን አካል ባለመኖሩ ወደህግ ለመሄድ መወሰናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በአሁን ወቅት ሞሃ በአዲስ አበባ የሚገኙ ሶስት ፋብሪካዎችን ጨምሮ በኢትዮጵያ በአጠቃላይ 8 የማምረቻ ፋብሪካዎች ያሉት ሲሆን በእነዚህ ድርጅቶች ውስጥ የሚገኙ ቁጥራቸው ጥቂት የማይባል ሰራተኞች በተለያዩ ጊዜያት ከስራ እንዲቀነሱ መደረጋቸው ተመላክቷል፡፡

አዲስ ማለዳ የሞሃ የለስላሳ መጠጦች ፋብሪካ አ.ማ በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጧት ደገግማ የጠየቀች ቢሆንም አልተሳካላትም፡፡ በቀጣይ የድርጅቱን ሃላፊዎች ምላሽ ስታገኝም ይዛ የምትቀርብ ይሆናል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here