የሚንስቴሩ ቃል አቀባይ ነቢዩ ተድላ እንደተናገሩት በቅርቡ ሱማሊያ ውስጥ ሲዘዋወር በጎሳ ታጣቂዎች የተዘረፈው ጦር መሳሪያ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያገናኘው አንዳች ነገር የለም ማለታቸውን አዲስ ማለዳ አሰምታለች፡፡
ሱማሊያ ውስጥ የጦር መሳሪያ ምዝገባ አያያዝ እና ሥርጭት ጉዳይ የሞቃዲሾ መንግሥት ኃላፊነት እንደሆነ የገለጹት ቃል አቀባዩ ጉዳዩ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የሚያገናኘው አንዳች ነገር የለም ብለዋል፡፡
በቅርቡ የሶማሊያ መንግስት የጦር መሳሪያዎች በኢትዮጵያ በኩል በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ የያዝኳቸው ነው ሲል ያቀረበውን ክስም መሰረተ ቢስ ብለውታል አምባሳደሩ፡፡
ከሳምንት በፊት ድርጊቱ የተፈፀመው ከአቡድዋክ ከተማ በስተሰሜን ምዕራብ ሽላ ማዶ በተባለ ቦታ ነው ሲል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የገለጸው የሱማሊያ ደህንነት ሚኒስቴር መሳሪያዎቹ ወደ ሀገር ውስጥ የገቡት በህገ ወጥ የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪዎች ነው ብሏል።
በመሆኑም ኢትዮጵያን ከጉዳዩ ጋር የሚያገናኛት አንዳችም ነገር የለም ያሉት ቃል-አቀባዩ ይህ የሱማሊያ የውስጥ ጉዳይ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያና ሱማሊያ ከገቡበት ዲፕሎማሲያዊ ቅራኔ ቁርሾ ጋር በተያያያዘ በተለይም የሞቃዲሾ መንግስት በተደጋጋሚ በድንበር አካባቢዎች ጥቃት እየደረሰብኝ ነው ሲል የሚደመጥ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስት ግን ክሱን መሰረተ-ቢስ ሲል አጣጥሎታል፡፡



