ሐምሌ 22 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ ) በሲዳማ ክልል ባጋጠመው የመሬት መንሸራተትና ደራሽ ውኃ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 11 መድረሱን የክልሉ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።
በክልሉ ወንሾ ወረዳ ባጋጠመ የመሬት መንሸራተት አደጋ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 9 መድረሱንና 6 ተጨማሪ ሰዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸው በይርጋለም ሆስፒታል በሕክምና ላይ መሆናቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል።
በተመሳሳይ በክልሉ ቡራ ወረዳ በደራሽ ውኃ የ2 ህጻናት ሕይወት ማለፉን ኮሚሽኑ ገልጾ፤ ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ መልዕክት አስተላልፏል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖች የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልጸው፤ ለሟች ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች መጽናናትን ተመኝተዋል።
የክልሉ መንግሥት በዜጎች ላይ ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ እንዲሁም ተጎጂዎች ሕክምና እና ድጋፍ እንዲያገኙ ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰራ ነው ብለዋል።
በሌሎች አካባቢዎችም መሰል ችግሮች ሊፈጠሩ ስለሚችሉ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ርዕሰ መስተዳድሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።



