‹‹አሁን ላይ ተስፋችን ሙሉ በሙሉ ተሟጧል›› የመቀለ ዩኒቨርሲቲ ሰራተኞች

አርብ ነሐሴ 03 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የመቀለ ዩኒቨርሲቲ ሰራተኞች የ17 ወራት ውዝፍ ደሞዝ አልተከፈለንም በሚል ላለፉት በርካታ ወራት እያሰሙ የቀጠሉት ጥያቄአቸው አሁንም መልስ አለማግኘቱን ገልጸዋል ፡፡

ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸውን የሰጡ አንድ የዩኒቨርሲቲው መምህር ‹‹ተስፋችን ሙሉ በሙሉ ተሟጧል›› ያሉ ሲሆን ኑሮ አቀበትን እንደመውጣት ከብዶናል ከዚህ በኋላም እንዴት መቀጠል እንደምንችል አናውቅም ብለዋል፡፡

እየቀረቡ ያሉ ጥያቄዎች በተናጠል መሆናቸው መብታችንን እንድናስከብር አላደረገንም የሚሉት እኚህ መምህር ጥያቄአችንን ለማስመለስ እኔ እስከማውቀው ድረስ የተቋቋመ ኮሚቴ የለም ብለዋል፡፡

አዲስ ማለዳ መሰል ጥያቄን ያነሳችላቸው አንድ የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደር ሰራተኛ ደግሞ ከወራት በፊት ከመምህራንና ከአስተዳደር ሰራተኞች የተውጣጣ ኮሚቴ ተቋቁሞ እንደነበር አስታውሰው አሁን ላይ ግን ኮሚቴው በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ እንደማያውቁ ይገልጻሉ፡፡

በጦርነት ውስጥ አሳልፈንና ከባድ ችግርን አይተን እንደመምጣታችን እንደነዚህ አይነት አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ምላሾች በቶሎ ሊሰጡን ይገባ ነበር በማለት ‹‹ተረስተናል›› ሲሉ የክልሉንና የፌድራሉን መንግስት ተጠያቂ አድርገዋል፡፡

የመቀሌ ዩንቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ተካቡ ገብረስላሴ በበኩላቸው ችግሩ ስር መስደዱን አንስተው መንግስትም ይሁን ክልሉ አሰቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጧቸው መጠየቃቸው አይዘነጋም፡፡

የዩኒቨርሲቲው መምህራንና አንዳንድ የአስተዳደር ሰራተኞች በኑሮ ውድነት የተነሳ በዩኒቨርሲቲው ባሉ የተማሪዎች መኝታ ቤት አስከመጠቀም መድረሳቸው መነገሩ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here