እሁድ ነሐሴ 05 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ)
1. የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት “በልዩ ሁኔታ” መስጠቱን ነሐሴ 03 ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።ይህን ተከትሎ የትግራይ ክልል ጊዜዓዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው እረዳ የምዝገባ ጥያቄውን የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ የማያውቀው ነው ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
2. የኢትዮጵያ መንግሥት በቀጣዩ ዓመት ታኅሳስ የእፎይታ ጊዜው የሚጠናቀቀው የ1 ቢሊዮን ዶላር ዩሮ ቦንድ ዋጋ በ20 በመቶ እንዲቀንስለት ሊጠይቅ እንደሆነ ተሰምቷል። ጥያቄው አበዳሪዎች ሙሉውን ብድር በረጅም ጊዜና በአነስተኛ ወለድ መልሰው ለማግኘት ባለፈው ታኅሳስ ላይ ለመንግሥት ካቀረቡት ሃሳብ ተቃራኒ እንደኾነ ተመላክቷል።
3. አባይ የጥበቃ አሰሪዎች ማህበር ቀደም ሲል የውጭ አገር ዜጎች በሕገ ወጥ መንገድ ቢሮ ከፍተው እየሰሩ ነው በሚል በመገናኛ ብዙሃን መግለጫ በመስጠት እንዲሰራጭ ያደረገው መረጃ ሃሰተኛ መሆኑን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡ለሙሉ ዘገባ፡ https://addismaleda.com/archives/38523
4. የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ለሚሰጣቸው የፓስፖርት አገልግሎቶች ክፍያ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ አድርጓል፤ በዚህም መሠረት አዲስ ፓስፖርት ለማውጣት በመደበኛ 5 ሺህ፣ በአምስት ቀን ለማውጣት 20 ሺህ ብር ሲሆን በሁለት ቀን አስቸኳይ ለማውጣት ደግሞ እስከ 25 ሺህ ብር ድረስ የአገልግሎት ክፍያ ያስከፍላል።
5. የኢትዮጵያ ህዝቦች አቢዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) ዋና ጸሃፊ ደስታ ጥላሁን ከፓርቲው መልቃቸውን ገልጸዋል፡፡በተለያዩ ወቅቶች የምሰነዝራቸውን አስተያየቶችና የማቀርባቸውን ሃሳቦች የፓርቲው ከፍተኛ አመራር ከመቀበል ይልቅ በቸልተኝነት ማለፍን መርጧል ሲሉ የወቀሱት ወ/ሮ ደስታ በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ስራቸውን መስራት አዳጋች እንደሆነባቸው ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል፡፡
6. ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎች ጋር መንግሥት ተከታታይ የሆነ ንግግር እያደረገ መሆኑን መናገራቸውን ተከትሎ፤ አዲስ ማለዳ ይህን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር እንዴት ተመለከታችሁት ስትል ጥያቄ ያቀረበችላቸው የተቀዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ድርድር መናገራቸው በጎ ቢሆንም አጠቃላይ ሂደቱን በተመለከተ የሰጡት ማብራሪያ ግን ግልጽነት የጎደለው ነው ብለዋል፡፡ለዝርዝሪ https://addismaleda.com/archives/38468
7. በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሺያን በሚመለከት በቅርቡ በሰጡት ማብራሪያ ላይ በኦሮሚያና አማራ ክልል ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ሃይሎች ጋር መንግስታቸው ድርድር መጀመሩን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ማብራሪያውን ተከትሎ ምላሽ የሰጡትና ከፋኖ አደረጃጀት መሪዎች አንዱ የሆኑት አቶ ዘመነ ካሴ ከብልጽግና መንግስት ጋር የተደረገ ምንም አይነት ድርድር የለም ብለዋል፡፡ለዝርዝር መረጃ https://addismaleda.com/archives/38474
8 የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ የፌደራል መንግሥት 551 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚያቀርብ ተናግረዋል፡፡በበጀት መልክ ለፓርላማ ከሚቀርበው ግማሽ ትሪሊዮን ብር ውስጥ 240 ቢሊዮን የሚሆነው ለማኅበራዊ ድጋፍ፣ለሴፍቲኔት፣ለሠራተኛ ደመወዝ ጭማሪ፣ ለመድኃኒት ድጎማ፣ ለዘይት ድጎማ፣ ለነዳጅ ድጎማ የሚውል መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
9. በኮሜርሻል ኖሚኒስ በኩል ለኢትዮጲያ ንግድ ባንክ ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞችን ለመቀነስ እቅድ ተይዟል መባሉ ተከትሎ በጉዳዩ ላይ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የኢትዮጲያ ንግድ ባንክ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አልሰን አሰፋ የሰራተኞች ጉዳይን በሚመለከት በተለይም በጽዳት፣መስተንግዶና መሰል አገልግሎት ላይ የሚሰሩ ሰራተኞችን ቅጥር የምንፈጽመው በኮሜርሻል ኖሚኒስ በኩል ነው ብለዋል፡፡ለዝርርዝሩ https://addismaleda.com/archives/38478
10. የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ታዬ ደንደአን ፍርድ ቤቱ ከቀረቡባቸው ሦስት ክሶች መካከል በ1ኛ እና በ2ኛ ክስ ነጻ የተባሉ ሲሆን ከጦር መሳሪያ ጋር ተያይዞ የቀረበባቸውን ክስ እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቷል፡፡
11. ከወራት በፊት የተገደሉት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የፖለቲካ ኦፊሰር አቶ በቴ ኡርጌሳ ወንድም እና ከግድያው ጋር በተያያዘ በእስር ላይ የሚገኙ 11 ሰዎች እንዲፈቱ አለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት ሂዩማን ራይትስ ዎች ጠይቋል።
12. በወላይታ ዞን ካዎ ኮይሻ ወረዳ ጤፓ ቀበሌ ዛሬ ረፋድ 5 ሠዓት አካባቢ በተከሰተ የመሬት ናዳ አደጋ የ11 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተሰምቷል፡፡በተከሰተው አደጋ እስካሁን በተደረገ ፍለጋ የ11 አስከሬን የተገኘ ሲሆን የሟቾች ቁጥር ሊያሻቅብ እንደሚችል የካዎ ኮይሻ ወረዳ አስተዳደር አሳውቋል።


