ረቡዕ ነሐሴ 15 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ)የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የ7 ዓመት ልጇን ሔቨን በግፍ ተነጥቃ ባለፈው አንድ ዓመት ተገቢ ፍትህ ሳታገኝ ለቆየችው ሲስተር አበቅየለሽ የከተማ አስተዳደሩ አንድ የመንግስት የመኖሪያ ቤት እንዲሁም በሙያዋ እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ እንድትሰራ መመቻቸቱን ገልጸዋል።
የፍትህ ሂደቱን ለመከታተል ፣ ያለችበት ሁኔታ የተሻለ እንዲሆንላት እና ተጋላጭነቷን ለመቀነስ እንዲመች የከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ ማድረጉንም ነው የገለጹት።
“የህፃን ሄቨን ጉዳይ የሁላችንም ጉዳይ በመሆኑ ድርጊቱ ተገቢውን ፍትህ ማግኘቱ የሌሎች ህፃናት ተጋላጭነትን ለመቀነስ አስተዋፅዖ ያለው ነው” ሲሉም ከንቲባዋ ተናግረዋል።
አክለውም፥ የዚህ አይነት ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት እንዳይፈፀም የማህበረሰቡ የአመለካከት ለውጥ እንዲመጣ እና ችግሩ የጋራ ጉዳይ በመሆኑ ሁላችንም ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል ማለታቸውን አዲስ ማለዳ ሰምታለች።



